ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ ከአፍሪካ አገራት ጋር ዲፕሎማሲዋን ማጠናከር አለባት

93

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ በአፍሪካ አገራት ላይ የዲፕሎማሲ ስራዋን አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት ምሁራንና ፖለቲከኞች ተናገሩ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

ፕሮፌሰር መረራ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኢትዮጵያ ግብፅ የምታደርገውን ዓለም አቀፍ ጫና ለመመከት በአፍሪካ ሀገራት ላይ የዲፕሎማሲ ስራዋን አጠናክራ መቀጠል አለባት

"የህዳሴው ግድብ ጉዳይ በቀዳሚነት የሚመለከተው ሶስቱን ሃገራት (ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን) ሲያልፍም አፍሪካዊያንን ነው" ያሉት ፕሮፌሰሩ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በብዙ የአፍሪካ ሃገራት የሚደገፍ ነው ብለዋል።

የሶስቱን ሃገራት ጉዳይ ከአፍሪካውያን ውጭ አሳልፎ መስጠት ከፍትሃዊነቱ ይልቅ ጉዳዩ ለፖለቲካ አጀንዳነት እንዲውል ያደርገዋል ነው ያሉት።

ከሶስቱ ሃገራት ባለፈ ለቀጠናውና ለአህጉሪቱ ሰላም እንደማይጠቅም ተናግረው ኢትዮጵያ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው አፍሪካዊያን ጋር የዲፕሎማሲ ትስስሯን ልታጠናክር ይገባታል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የሃገር ውስጥ ፖለቲካውን በማስተካከል በብሄራዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ያለውን አንድነት ማጠናከር ያስፍልጋል ብለዋል።

በሃገር ውስጥ ባሉ ፖለቲከኞች መካከል ምንም አይነት የሃሳብ ልዩነት መንሸራሸሩ የዴሞክራሲ መገለጫ ቢሆንም ህዝብን፣ ሃገርንና ሉአላዊነትን አደጋ ላይ በሚጥል ጉዳይ ላይ ግን ልዩነት መኖር የለበትም ብለዋል።

የሰብዓዊ መብት ተጋቹ ኦባንግ ሜቶ እንዳሉትም በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ያላካተተ የቅኝ ገዥዎች ስምምነት በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም።

በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንዲህ አይነት ተግባራትን ለማስቀጠል መሞከርም ከሰብአዊነት ያለፈና ኢትዮጵያ የማትቀበለው መሆኑን አብራርተዋል።

ግድቡ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን እንደመሆኑ በተጠቃሚነት ጉዳይ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በጥብቅ የሚመለከተው መሆኑንም ገልጸዋል።

ከ60 በመቶ በላይ ዜጎቿ በጨለማ ውስጥ የሚኖሩባት ኢትዮጵያ ግድቡን እየገነባችው ያለው የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት መሆኑ ይታወቃል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አፈፃፀም አሁን ላይ 73 ነጥብ 7 በመቶ ደርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም