በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋጁን የተላለፉ ከአንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ በላይ ግለሰቦች ተቀጡ

67

አሶሳ፣ ግንቦት 22/2012 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የክልከላ ድንጋጌዎችን ተላልፈዋል የተባሉ ከአንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ በላይ ግለሰቦች መቀጣታቸውን የክልሉ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ።

የግብረ ኃይሉ አባልና  የክልሉ የጸጥታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ኮማንደር አብዱላዚዝ መሃመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት ወረርሽኙን ለመከላከል ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር   እጅ መታጠብና አለመጨባበጥ  ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡

ሆኖም  ግንዛቤው  እያላቸው የሚዘናጉ ሰዎች  ቁጥር አሁንም ከፍተኛ  መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ በሻይ ቡና፣ ሆቴሎች እና ሌሎች ቦታዎች አካላዊ ርቀታቸውን ሳይጠብቁ ሲገለገሉና አገልግሎቱን ሲሰጡ የነበሩ ጨምሮ  276 ሰዎች በገንዘብ መቀጣታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ትርፍ የጫኑ 770 የመለስተኛ ህዝብ ማመላለሻ፣ ባጃጅ እና ሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች እያንዳንዳቸው እስከ ሶስት ሺህ ብር ቅጣት እንደተጣለባቸው አስረድተዋል፡፡

ያልተገባ ዋጋ በመጨመር የተደረሰባቸው 448 ነጋዴዎች ደግሞ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ታይቶ እያንዳንዳቸው እስከ አራት ሺህ ብር እንደተቀጡ  አመልክተው "12 ነጋዴዎች ደግሞ ፈቃዳቸው ተሰርዟል "ብለዋል፡፡

ሌሎች 459 ደግሞ በመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መታለፋቸውን ኮማንደር አብዱላዚዝ ገልጸዋል፡፡

ሰርግ በማዘጋጀት  በርካታ ሰዎች እንዲታደሙ ያደረጉ አራት የመተከል ዞን ነዋሪዎች በፍርድ ቤት ውሳኔ እያንዳንዳቸው በስድስት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ለአሶሳ ከተማ ህዝብ የመጣ ሰባት ኩንታል ስኳር ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ ሁለት ግለሰቦችም እያዳንዳቸው በአስር ወራት እስራት እንዲቀጡ በፍርድ ቤት መወሰኑን ኮማንደሩ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም