የአምነስቲ ኢንተርናሽናል መግለጫ የተሳሳተና ሚዛናዊነት የጎደለው ነው... የኦሮሚያ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ

54

አዲስ አበባ ግንቦት 22/2012 (ኢዜአ) አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው ሪፖርት ሚዛናዊነት የጎደለውና የተሳሳተ መሆኑን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው እንዳለው "አምንስቲ ኢንተርናሽናል ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በመንግስት ኃይሎች የተፈጸመ የሰብአዊ መብት ጥሰት አለ" ብሏል።

ይሁን እንጂ ሪፖርቱ ሚዛናዊነት የጎደለውና የተሳሳተ መሆኑን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል።

"ሪፖርቱ የአንድ ወገን መረጃን ብቻ የያዘ፣ ሚዛኑን ያልጠበቀና የተሳሳተ በመሆኑ ሊታረም ይገባል" ብለዋል።

ሪፖርቱ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ መሆኑን ያስታወሱት ኃላፊው በተለይ ነፍጥ ያነገቡ ታጣቂዎች በተለያዩ አካባቢዎች በሕዝብና በመንግስት ኃይሎች ላይ የሚፈፅሙትን ወንጀል መካዱን አስታውቀዋል።

"በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰብዓዊ መብት ላይ እየሰራ ያለ ድርጅት የአንድ ወገን ብቻ ሪፖርት ሰምቶ ከማንጸባረቅ ይልቀ ሚዛናዊና ተዓማኒ መረጃ መጠቀም ነበረበት" ብለዋል።

ለዚህም ድርጅቱ በሪፖርቱ ላይ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ አካባቢ 38 ሰዎች መገደላቸውንና ከእነዚህ ውስጥ 16 ሰዎች በመንግስት ኃይሎች የተገደሉ መሆኑን ከገለጸ በኋላ ስለሌሎቹ ሰዎች ምንም ሳይል ማለፉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

"ሪፖርቱ ሚዛናዊ ያልሆነና በተቃዋሚ ጎራ ያሉ ግለሰቦች የራሳቸውን ሀሳብ ያንጸባረቁበት በመሆኑ በመንግስት በኩል ተቀባይነት የለውም ብለዋል አቶ ጌታቸው።

በክልሉ ውስጥ ሰዎች በታጣቂዎች የተገደሉበት፣ የታገቱበትና የት እንደደረሱ የማይታወቅበት ሁኔታ ቢኖርም ሪፖርቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ያለማለቱንም ኃላፊው ጠቁመዋል።

ድርጅቱ ከመንግስት የወሰደው መረጃ አለመኖሩን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፣ ያወጣው ሪፖርት መንግስት የሰራቸውን ሥራዎች የሚያንቋሽሽ በመሆኑ እንደገና ሪፖርቱን ማጤን እንዳለበት ተናግረዋል።

"ሪፖርቱ መንግስትን ለመጉዳትና ሌላውን ወገን አጉልቶ ለማሳየት የተደረገ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም፤ ሊስተካከል ይገባል" ሲሉም ገልጸዋል።

"አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ከሆነ ሁሉንም ማካተት ነበረበት' ያሉት ሃላፊው፤፣ ያወጣው ሪፖርት ግን የአንድ ወገን ወገንተኝነት የታየበት መሆኑን አመልክተዋል።

"ድርጅቱ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ላይ የሚሰራ በመሆኑ ሁሉንም ያከተተ ሪፖርት ማውጣት ሲገባው በአቋራጭ ስልጣን ላይ ለመውጣት የሚፈልጉ ኃይሎችን ፍላጎት ያበረታታ ሪፖርት ነው" ብለዋል።

የክልሉም ሆነ የአገሪቱ ህዝብ በሪፖርቱ የተሳሳተ ግንዛቤ ሊይዙ አይገባም ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ድርጅቱ ከክልሉ መንግስት ተጨባጭ መረጃን ተጠቅሞ ሪፖርት የማድርግ ፍላጎት ካለው የክልሉ መንግስት ያለውን መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ መሆኑንም ነው ያረጋገጡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም