በዓድዋ ከተማ በ181 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቁ

71

አክሱም፣ ግንቦት 22/2012 (ኢዜአ) በዓድዋ ከተማ የነዋሪዎች ጥያቄ ለመመለስ እንዲያግዙ 181 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የተገነቡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቁ።

የከተማው አስተዳደር  ከንቲባ አቶ ሙሉጌታ ገብሩ ለኢዜአ እንደተናገሩት የከተማዋን የመሰረተ ልማት አቅርቦት ክፍተት ለመሙላት አስተዳደሩ  ስድስት የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ አካሂደዋል።

ለዚህም አስተዳደሩ 181 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጓል ብለዋል።

ተገንብተው አገልግሎት  ከበቁ መሰረተ ልማቶች መካከል ሶስት ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የጎርፍ ማውረጃ ቦዮችና ሶስት መለስተኛ ድልድይ ይገኙባቸዋል።

እንዲሁም ከአምስት ኪሎ ሜትር በላይ የድንጋይ ንጣፍ መንገድ፣ ሁለት የገበያ እና   ሁለት የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት   ተገንብተው ለአገልግሎት  በቅተዋል።

የመሰረተ ልማት ግንባታዎቹ  የነዋሪዎች የረጅም ጊዜ ጥያቄ ከመመለሳቸው ባሻገር በግንባታው ሂደት ለስድስት መቶ ወጣቶችም  የስራ እድል ፈጥረዋል ብለዋል።

በከተማዋ የምዕባለ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አለም መኮንን በሰጡት አስተያየት የከተማ የመሬት አቀማመጥ ተዳፋት  በመሆኑ የሳቸውን ጨምሮ የበርካታ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እንደነበሩ አውስተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ አሁን በገነባው የጎርፍ መውረጃ ቦይ ከጎርፍ አደጋ ስጋት ነጻ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

የዓዲማሕለኻ አካባቢ ነዋሪ ወይዘሮ አልማዝ ዘሚካኤል በበኩላቸው በከተማዋ ዘንድሮ የተሰሩ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

በአከባቢያቸው በተለይ በክረምት ወቅት ህጻናት እና አዛውንቶች በጎርፍ እና ጭቃ ምክንያት ለመሻገር ይቸገሩ  እንደነበር ተናግረዋል።

አሁን የከተማ አስተዳደሩ ድልድዮች  እና ቦዮች ገንብቶ ለአገልግሎት በማብቃቱ ስጋታቸው መቃለሉንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም