የትምህርትና ስልጠና ኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ተቋም ሊከፈት ነው

100
አዲስ አበባ ሰኔ 29/2010 የመማር ማስተማር ስርዓቱን ጥራት ለማሳደግ የሚያግዝ የትምህርትና ስልጠና ኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) ተቋም ለመክፈት ዝግጅት ማጠናቀቁን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። የመምህራን የማስተማሪያ ዘዴ በተንቃሳቃሽ ስልኮች ጭምር የታገዘ እንዲሆን የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችም ስራ ላይ ይውላሉ። ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ አዲስ የሚቋቋመው የአይሲቲ ተቋም የአገሪቱን ስርዓተ-ትምህርት መረጃና የምርምር ስርዓት ወቅታዊ በሆኑ ቴክኖሎጂዎች ለማስደገፍ የሚያስችል ነው። የተቋሙ ድርጅታዊ መዋቅር ጥናት የተጠናቀቀ በመሆኑ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ትምህርትን ጨምሮ የቴክኒክና ሙያ እንደዚሁም የከፍተኛ ትምህርት ዘርፎችን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ የሚደረገው ጥረት የሚከናወነው በተበታተነ መንገድ ነው። የተቋሙ መከፈት ይህንን ችግር በማስወገድ በትምህርቱ ዘርፍ ከአይሲቲ ጋር በተያያዘ የሚከናወኑ ተግባራት ተቋማዊ አደረጃጃት እንዲኖራቸውና የመማርና ማስተማር ሂደቱን ጥራት ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ሚኒስትሩ ገልፀዋል። ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ በአሁኑ ወቅት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚሰጠው 'ኋላ ቀር' በሆነ ቴክኖሎጂ ነው። በሬዲዮ አማካኝነት የሚሰጡ የትምህርት መርሃ-ግብሮች ኋላ ቀር በሆኑና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአገልግሎት ውጭ በተደረጉ የማስተማሪያ ዘዴዎች መሆኑን ጠቁመዋል። ሌሎች አገሮች የፕላዝማ ማስተማሪያ ቴክኖሎጂን ከማስተማሪያነት ባለፈ እንደ ሰሌዳ፣ ቤተ-ሙከራ፣ መለማማጃና ለሌሎች የማስተማሪያ ተግባራት እያዋሏቸው ቢሆንም በኢትዮጵያ ገና እዚህ ደረጃ ላይ እንዳልተደረሰ ሚኒስትሩ አቶ ጥላዬ ተናግረዋል። የአይሲቲ ተቋሙ መመስረት የሬዲዮና የፕላዝማ ቴክኖሎጂ ማስተማሪያ ዘዴዎች ሌሎች ያደጉ አገሮች የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል። ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ የትምህርት መሳሪያዎችና የቤተ-ሙከራ ግብዓቶችን ወጪ ለመቀነስ ያግዛል ተብሏል። የመምህራን የማስተማሪያ ዘዴ በተንቃሳቃሽ ስልኮች ጭምር የታገዘ እንዲሆን የሚችልበት ቴክኖሎጂ ስራ ላይ እንደሚውል ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። በሌላ በኩል ስርዓተ ትምህርት የማዘጋጀት፣ የመገምገምና የማሻሻል ዓላማ ያለው 'የስርዓተ-ትምህርት ጥናትና ምርምር ተቋም' ለማቋቋም የሚያስችል የመዋቅር ጥናት ተጠናቆ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀርብ እንደሆነ ዶክተር ጥላዬ አስታውቀዋል። ከዚህም ሌላ ተቋሙ አጋዥ ጽሁፎችና መጻህፍት የማዘጋጀት፣ በስርዓተ-ትምህርት ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን  የመስጠት ተልዕኮዎች ይኖሩታል። በአሁኑ ወቅት የትምህርት አጋዥ የሆኑ ድጋፍ ሰጪ መጻህፍት እየተዘጋጁ ያሉት በባለድርሻ አካላት ሳይሆን በዘርፉ በተሰማሩና ለትርፍ በሚሰሩ አካላት በመሆኑ የተጠያቂነት ክፍተቶች መኖራቸውን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። አብዛኛዎቹ አጋዥ መጻህፍት የጥራት መጓደል ችግሮች እንዳሉባቸውም ተናግረዋል። በቅርቡ የሚቋቋመው ተቋምም ከስርዓተ-ትምህርትና ከአጋዥ መጻህፍት ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመፍታት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ያግዛል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም