መንግስት ኢንዱስትሪ ፓርክ የመገንባት ድርሻውን እያጠናቀቀ ነው

80

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22/2012(ኢዜአ) መንግስት ኢንዱስትሪ ፓርክ የመገንባት ድርሻውን እያጠናቀቀ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ስድስት ኢንዱስትሪ ፓርኮች በግል ባለሃብቱ በመገንባት ላይ መሆናቸውም ታውቋል። 

ኢትዮጵያ እስከ 2013 መጨረሻ 30 ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ለመገንባት ዕቅድ ይዛለች።

ከነዚህ ውስጥ 15ቱ በመንግስት 15ቱ ደግሞ በግል ባለሃብቱ የሚገነቡ ናቸው።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ለሊሴ ነሜ ለኢዜአ እንደገለጹት መንግስት በአፋር ሰመራ ከተማ በመገንባት ላይ ያለውን ጨምሮ እስካሁን 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ገንብቷል።

ቀሪዎቹን በሚቀጥለው ዓመት ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙን የተናገሩት ወይዘሮ ለሊሴ ከዚያ ጎን ለጎን የግል ባለሃብቱ በኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ላይ እንዲሳተፍ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

 በመንግስት የተያዙ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ግል ዘርፉ ለማዘዋወር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

"ይህም የፓርኮቹን ትርፋማነት ለማጎልበትና መንግስት በሌሎች የመሰረት ልማት ሥራዎች ላይ እንዲያተኩር ያግዛል" ብለዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው እየተንቀሳቀሱ ካሉ ባለሃብቶች አብዛኞቹ ከኤዥያ ሲሆኑ ከአውሮፓና አሜሪካም የመጡ ይገኙበታል።

የአገር ውስጥ ባለሃብቶች በፓርኮቹ በስፋት እንዲሳተፉ ኮርፖሬሽኑ የተለያዩ ማበረታቻዎችን እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ይሁንና በዚህ ረገድ የሚፈለገው ውጤት አልመጣም ብለዋል።

የአገር ውስጥ ባለሃብቱን ለማበረታታት ከውጭ ባለሃብቶች ጋር በሼር እንዲሰሩ ማድረግ እንዲሁም የብድርና የማሽነሪ አቅርቦትን ማመቻቸት ይገኝበታል።

በአሁኑ ወቅት በቦሌ ለሚ፣ በኮምቦልቻ፣ በደብረ ብርሃን፣ በአዳማ እና በድሬዳዋ የግል ባለሀብቶች ኢንዲስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ላይ ናቸው።

ቀደም ሲል በዱከምና በአዲስ አበባ ዙሪያ ኢስተርን ውሃጃን የግል ኢንዱስትሪ ፓርኮችን መገንባታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም