ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች የሚልኩትን ገንዘብ ለሕዝብ ጥቅም እንዲውል በባንክ እንዲልኩ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጠየቁ

76
አዲስ አበባ ሰኔ 29/2010 በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ለአገራቸው የሚልኩትን ገንዘብ ለሕዝብ ጥቅም በሚሆን መልኩ በባንክ እንዲልኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጠየቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ በውጭ አገር ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ወደአገር ቤት የሚልኩትን ገንዘብ በባንክ በኩል እንዲልኩ ጥሪ አቅርበዋል። የውጭ ምንዛሬ በባንክ በኩል መላኩ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር በማስወገድ አገርና መንግስት የሚፈልገውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል። በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዳያስፖራው ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚውል የውጭ ምንዛሬ ለመላክ ቢፈልጉ የ'ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ' ተቋቁሞ ምንም ሳይቀነስለት በየቀበሌው ለትምህርት ቤት ግንባታና ለጤና ችግሮች መፍቻ የሚያገለግልበት አዲስ ሃሳብ አንስተዋል። በውጭ አገር ይኖራል ተብሎ ከሚገመተው አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ "በቀን ቢያንስ አንድ ዶላር በትረስት ፈንድ ቢያስገባ በወር 30 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሰብሰብ ይቻላል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከእያንዳንዱ ዳያስፖራ የምትሰበሰብ ቀላል ገንዘብ አገር ውስጥ ከፍተኛ ማህበራዊ ችግሮችን መፍታት እንደሚያስችል ተናግረዋል። በዚህም ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት በዚህ መልኩ ከተሰራ ምን ያህል አገራዊ ፋይዳ እንዳለው ዳያስፖራው እንዲታዘብ ነው ጥሪ ያቀረቡት። በሌላ በኩል "እያንዳንዱ ዳያስፖራ ለአገሩ አምባሰሳደር ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለአገሩ መልካም ስም እንዲሰራና በቱሪዝም መስክ ያለውን አቅም እንዲያስተዋውቅ ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካለምንም ፖለቲካዊ ልዩነት ለአገራዊ መልካም ስራዎች ዳያስፖራው ጥሪውን ተቀብሎ እንደሚተገብረውም እምነታቸውን ገልጸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም