ብሄራዊ የአረንጓዴ አሻራ ኮሚቴ በአዳማ ወረዳ ለመትከል ዝግጁ የሆኑ ችግኞችን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
ብሄራዊ የአረንጓዴ አሻራ ኮሚቴ በአዳማ ወረዳ ለመትከል ዝግጁ የሆኑ ችግኞችን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22/2012 (ኢዜአ) ብሄራዊ የአረንጓዴ አሻራ ኮሚቴ አባላት በአዳማ ወረዳ ለመትከል ዝግጁ የሆኑ ችግኞችን ጎበኙ።
ብሄራዊ የአረንጓዴ አሻራ ኮሚቴ አባላት በአዳማ ወረዳ ሶደሬ ቀበሌ እየተከናወኑ የሚገኙ የችግኝ ማፍላት ተግባራትን ጎብኝተዋል።
ኮሚቴው ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ታዋቂ ግለሰቦችን በማካተት መዋቀሩ ይታወቃል።
ኮሚቴው የአካባቢው ወጣቶች በማህበር በመደራጀት ያፈሏቸውንና ለመተከል ዝግጁ የሆኑ የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን ችግኞች በዛሬው እለት ጎብኝቷል።
ችግኞቹ የተዳቀሉ የማንጎ ዝርያዎችን ጨምሮ ሌሎች የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ሲሆኑ በኮሚቴው ተጎብኝተዋል።
የማንጎ ችግኞቹ 45 ሺህ ሲሆኑ በማህበር በተደራጁ ወጣቶች የተዘጋጁና ለወጪ ንግድ የሚውሉ ምርቶችን ለማግኘት የሚያስችሉ መሆናቸው ተገልጿል።
ኮሚቴው በመቀጠል በሞጆ ከተማ መሰል ጉብኝት እንደሚያደርግ በስፍራው የሚገኘው የኢዜአ ሪፖርተር ያደረሰን መረጃ ያሳያል።
ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ርዕሰ ብሔሯን፣ ርዕሰ መንግሥቱን፣ እንዲሁም የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ በተሳተፉበት የችግኝ ተከላ፣ ብሔራዊ አስተባባሪው ኮሚቴ በዕለቱ እንዳስታወቀው 23 ሚሊዮን ሕዝብ ባደረገው ተሳትፎ 353 ሚሊዮን 633 ሺህ 660 ችግኞችን በአንድ ቀን ተክሏል፡፡
ለተከላው በዕቅድ ተይዞ ከነበረው 200 ሚሊዮን ችግኞች በ75 በመቶ ብልጫንም አሳይቷል፡፡
ይህም ህንድ ከዓመታት በፊት 60 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ቀን በመትከል በጊነስ ወርልድ ቡክ ያስመዘገበችው ክብረ ወሰን በኢትዮጵያ ‹‹መሰበሩን›› አስተባባሪ ኮሚቴው መግለጹ ይታወሳል።