በትግራይ በሁለት ከተሞች የተጀመሩ ሆስፒታሎች ግንባታ በመጓተቱ ቅሬታ አስከተለ

89

አክሱም/ማይጨው፣  ግንቦት 21/2012ዓ.ም /ኢዜአ/ በትግራይ ክልል ከአራት ዓመታት በፊት የተጀመሩ ሁለት ሆስፒታሎች ግንባታቸው በመጓተቱ ምክንያት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር እየፈጠረ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለፁ ።

ግንባታቸው የተጓተተው ሆስፒታሎች የዓድዋ አጠቃላይ ሆስፒታልና የዓዲሻሁ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ናቸው ተብሏል ።

የዓድዋ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ክንፈ ገብረ እግዛብሄር ለኢዜአ እንደተናገሩት የአገልግሎት አሰጣጡን ዘመናዊ ለማድረግና ለማስፋፋት ታስቦ  ፕሮጀክቱ በ2008 ዓ.ም በ280 ሚሊዮን ብር ወጪ የተጀመረ ነው ።

በተያዘለት እቅድ መሰረት ዘንድሮ መጠናቀቅ ሲገባው እስከ አሁን ድረስ የተከናወነው ግን 55 በመቶ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል ።

አገልግሎት ፈላጊው የህብረተሰብ ክፍል ቁጥሩ እየጨመረ በመምጣቱ በስራ ላይ ያለው ህንፃ ያረጀ በመሆኑ ግንባታው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ጠይቀዋል።

 የዓድዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙሉጌታ ገብሩ በበኩላቸው የሆስፒታሉ ግንባታ  በተደጋጋሚ በመቋረጡ በህብረተሰቡ ላይ ቅሬታ መፍጠሩን ገልፀዋል ።

የዓድዋ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ መብርሂት አድሓኖም በሰጡት አስተያየት በግንባታው መጓተት ህዝቡ በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ቢያሰማም መፍትሔ ግን አላገኘም ብለዋል ።

ግንባታውን የሚያከናውነው ዛምራ የህንጻ ተቋራጭ የግል ማህበር  የፕሮጀክቱ ማናጀር አቶ ብርሃነ ወልደ ኪሮስ ስለ ሁኔታው ተጠይቀው ግንባታው የተጓተተው  ወቅቱን ጠብቆ ክፍያ ስለማይፈፀምላቸው ነው ።

በተመሳሳይ በአላጀ ወረዳ አዲሽሁ ከተማ በ40 ሚሊዮን ብር በጀት በ2010 ዓም የተጀመረው የዓዲ ሽሁ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ዘንድሮ መጠናቀቅ ሲገባው በመጓተቱ ምክንያት ቅሬታ እንዳደረባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልፀዋል ።

የወረዳው የጤና ባለሙያ አቶ አታክልቲ ሀይሉ እንደገለጹት የሆስፒታሉ ግንባታ 15 በመቶ ከደረሰ በኋላ ግንባታው ከተቋረጠ ሶስት ዓመት ሆኖታል ።

ሆስፒታሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ባለመብቃቱ ምክንያት በወረዳው የሚገኘው ጤና ጣብያ በቀን እስከ 300 ተገልጋዮች ለማስተናገድ መገደዱን ተናግረዋል።

የዓዲሻሁ ከተማው ነዋሪ አቶ ደስታ መንግስቱ በበኩላቸው ሆስፒታሉ ይሰራል ብለን ተስፋ አድርገን የነበረ ቢሆንም ግንባታው በመቆሙ ቅሬታ አድርብናል ብለዋል ።

የአላጀ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ረዳኢ ብርሀኑ እንደገለፁት ግንባታው  የተቋረጠው ከኮንስትራክሽን ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ ህንፃ ተቋራጩ ለኪሳራ በመዳረጉ መሆኑን ገልፀዋል ።

አዲስ ጨረታ በማውጣት ግንባታው ለማስቀጠል ዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የክልሉ ኮንስራክሽን የመንገድናትራንስፖርት ቢሮ የፕሮጀክቶች ግንባታ ምህንድስና ዲዛይን ባለሙያ አቶ መዝገበ አብርሃ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት መልስ በሂደት የሆስፒታሉ ዲዛይን መቀየሩ ለመጓተቱ አንዱ ምክንያት ነው ብለዋል ።

የዲዛይን ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ ደግሞ በህንጻ ተቋራጩ አቅም ማነስ ችግር ምክንያት በወቅቱ የተመደበው በጀት ሳይጠቀምበት የበጀት አመት በመድረሱ ወደ ሌላ ፕሮጀክት እንዲዞር ተደርገዋል ብለዋል።

አሁን ደግሞ በበጀት እጥረት ምክንያት ግንባታው መስተጓጎሉን ተናግረዋል።

ሁለቱም ሆስፒታሎች በቀጣይ  አመት አስፈላጊውን በጀት እንዲያዝላቸው በማድረግ ለማጠናቀቅ ጥረት እንደሚደረግ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም