በአዳማ ከተማ ክልከላዎችን የተላለፉ 766 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

38

አዳማ፤ ግንቦት 21/2012 (ኢዜአ ) በአዳማ ከተማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የክልከላ ድንጋጌዎችን ተላልፈው ተገኝተዋል የተባሉ 766 ግለሰቦችን ፖሊስ  በቁጥጥር ስል ማዋሉን አስታወቀ። 

በከተማው የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባልና የአዳማ  ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ረዳት ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልሜቻ  ለኢዜአ እንደገለፁት ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት የአዋጁን ክልከላዎች ተላልፈው በተለያዩ አካባቢዎች  ተሰባስበው እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል  ሳያደርጉ በመገኘታቸው ነው።

ግለሰቦቹ የተገኙት በቤተ እምነቶች ፣ በጫት ቤት፣ በመጠጥ ቤት፣ በፑል ቤቶች፣ በትራንስፖርትና ገበያ አካባቢዎች መሆኑን አመልክተዋል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል 136  የሚሆኑት በምክር የተለቀቁ ሲሆኑ ስድስት መቶ ሰላሳ የሚሆኑት ፍርድ ቤት መቅረባቸውን አስረድተዋል።

በተመሳሳይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያ ጥስው የተገኙ አንድ ሺህ አርባ ዘጠኝ አሽከርካሪዎች ከሁለት ሺህ እስከ አምስት ሺህ ብር መቀጣታቸውን ረዳት ኢንስፔክተሯ ጨምረው ገልፀዋል።

አሽከርካሪዎቹ  የተቀጡት ትርፍ በመጫንና  ከታሪፍ በላይ በማስከፈላቸው እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም