የአስተዳደሩ የሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት በአዲስ መልክ ተደራጀ

128

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዛሬ በአዲስ መልክ ተደራጀ።

ምክር ቤቱ በአዲስ መልክ የተደራጀው የአስተዳደሩ ነዋሪዎች በግድቡ ግንባታ የተፈጠረውን ብሔራዊ መግባባትና መነሳሳት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር መሆኑም በስብሰባው ላይ ተገልጿል።

ምክር ቤቱ ሕዝቡ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን ተሳትፎ በማጠናከር የሀብት አስባሰብም ሆነ ሌሎች የንቅናቄ ሥራዎችን ወደ ላቀ ደረጃ እንዲያደርስ ተልዕኮ ተሰጥቶታል።

በአዲስ መልክ የተቋቋመው ምክር ቤት ዘጠኝ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት አሉት።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ኢንጂነር እንዳወቅ አብጤ የምክር ቤቱ ስብሳቢ፤ የአዲስ አበባ ከተማ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘመን ጁነዲ ደግሞ ምክትል ሰብሳቢ ሆነዋል።  

ኢንጂነር እንዳወቅ በዚሁ ወቅት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን እየተከላከሉ ለግድቡ ግንባታ የሚደረገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ማሳደግ አለብን ብለዋል።

ግድቡ የኢትዮጵያዉያን የታላቅነት መገለጫ በመሆኑ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።

የመንግሥትም ሆነ የምክር ቤቱ አመራር የግድቡን ግንባታ ጉዳይ ከመደበኛ ሥራው ጋር አስተሳስሮ ማከናወን ይገባዋል ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ ናቸው።

ልዩነትን ወደ ጎን በመተው በአንድነት ሆነን ግድቡን ማጠናቀቅ አለብን ሲሉም አስገንዝበዋል።

የምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የግድቡ ባለቤት የሆነውን ሕዝብ ተሳትፎ ለማጎልበት እንደሚሰሩ በዚሁ ወቅት ተናግረዋል።

የግድቡ ግንባታ 73 ነጥብ 7 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም