የመሥሪያ ቦታ ችግር እንዲፈታላቸው በሀዋሳ በወተት ላምች እርባታ የተሰማሩ ማኅበራት ጠየቁ

148

ሐዋሳ ፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) ያጋጠማቸውን የመሥሪያ ቦታ ችግር እንዲፈታላቸው በሀዋሳ ከተማ በወተት ላሞች እርባታ የተሰማሩ ማኅበራት ጠየቁ።

በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የተመራ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ  የግብርና ልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል።

በዚህ ወቅት የሙሉ እና ቤተሰቦቿ የወተት ከብት እርባታ ማኅበር ሰብሳቢ ወይዘሮ መሉ ጎሽሜ እንዳሉት ማኅበሩ በ2008 ዓ.ም 60 ሺህ ብር በሆነ ካፒታል ሲመሠረት አንድ የወተት ላም ብቻ  ነበረው።

አሁን ላይ የወተት ላሞችን ቁጥር 50 በማድረስ በቀን እስከ 200 ሊትር ወተት ለገበያ እያቀረቡ አንደሚገኙ ተናግረዋል።

በሂደት  ካጋጠማቸው  ችግሮች መካከል ለመኖ ማከማቻ፣ ቆሻሻ ማስወገጃና ጥጆች የሚያስሩበት የቦታ ጥበት በሥራቸው ላይ ከፍተኛ  ጫና እንዳሳደረባቸው አመልክተዋል።


ወይዘሮ ሙሉ ለራሳቸውና ለልጆቻቸው የሥራ ዕድል ከመፍጠራቸውም ባለፈ በቋሚነትና ጊዚያዊ የጉልበት ሠራተኝነት በሥራቸው የሚተዳደሩ ብዛት ያላቸው ሰዎች እንዳሏቸው ገልጸዋል።


ከአንድ ሚሊዮን 800 ሺህ ብር በላይ ካፒታል ማፍራታቸውን የጠቆሙት ወይዘሮ ሙሉ አሰራራቸውን የማዘመንና በሰፊው የመሥራት ዕቅድ እንዳላቸውም አስታውቀዋል።


ልማታቸውን  በማስፋፋት ይበልጥ ራሳቸውንና ሌሎችን ይበልጥ ተጠቃሚ ማድረግ እንዲችሉ ከተማ አስተዳደሩ  ያለባቸውን የመሥሪያ ቦታ ችግር በመፍታት እንዲያግዛቸው ጠይቀዋል።

የሙቤ የወተት ከብት እርባታ ማኅበር ሰብሳቢ ሀጂ መሀመድ ይመር በበኩላቸው ከአራት ዓመት በፊት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተደራጅተው ልማት ውስጥ  ሲገቡ  የነበራቸውን ስድስት የወተት ላሞች ወደ 17 ማሳደግ እንደቻሉ ተናግረዋል።


እንደ ሀጂ መሀመድ ገለጻ ማኅበሩ ካለበት የቦታ ጥበት ባለፈ ቤቱም ለእርባታ ሥራው አመቺ  ባለመሆኑ ሥራቸውን ለማስፋፋት እንቅፋት እንደሆነባቸው አመልክተዋል።

"ያለንን አቅም ተጠቅመን አስፋፍትን መሥራት እንድንችል የከተማ አስተዳደሩ ያሉብንን የቦታ ችግር  እንዲፈታልን እንጠይቃለን " ብለዋል።


የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ  የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በልማት ላይ እየፈጠረ ያለውን ጫና ለመቀነስ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የግብርና ሥራዎችን በትኩረት ለመደገፍ በማስፈለጉ ጉብኝት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።


በከተማዋ 15 በወተት ላሞች እርባታ የተሰማሩ ማኅበራት እንዳሉ ጠቅሰው  የግብርና ልማት ሥራ ከተማ ውስጥ ውጤታማ መሆን እንደሚችል  ማኅበራቱ በተግባር  ማሳየታቸውን አረጋግጠዋል።

ማኅበራቱ  በቀን እስከ 2 ሺህ 500 ሊትር ወተት በማምረት የከተማውን  ሕዝብ የወተት ፍላጎት እየሸፈኑ እንደሚገኙ ገልጸው በሥራቸው ለሚገኙ ብዛት ያላቸው ሰዎችም የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን አስታውቀዋል።


ማኅበራቱ ያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢነት ያላቸው በመሆኑ  ያሉባቸውን ችግሮች የከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።


ማኅበራቱ የፈጠሩት ካፒታል ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሊያሸጋግራቸው እንደሚችል  ጠቁመው በተለይ በአንድ ላይ ሆነው የኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒዮን በማቋቋም ማሽኖችን ተጠቅመው ወተት ወደ ማቀነባበር እንዲገቡ ከተማ አስተዳደሩ የመሬትና ብድር አቅርቦት እንደሚያመቻችላቸው አብራርተዋል።


በምክትል ከንቲባው  የተመራው የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በከተማዋ በመጪው ሐምሌ ወር የሚተከል ችግኝ ዝግጅትንም ተመልክተዋል።     

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም