የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ወደ ምዕራብ ጎንደር ዞን ድጋፍ ሰጪ የሕክምና ቡድን ላከ

57

መተማ ፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ)  በምዕራብ ጎንደር ዞን ለይቶ ማቆያ ማዕከላት የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት መስፋፋትን ተከትሎ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ቋሚ ድጋፍ የሚያደርግ የሕክምና ቡድን ወደ ቦታው ላከ።

የሕክምና ቡድኑ መሪው አቶ አሻግሬ ገበየሁ  እንደገለጹት  ቡድኑ  ወረርሽኙን  ለመከላከል  ዞኑ እያደረገ ያለውን ጥረት የሚደግፍ ነው።

ስምንት አባላት ያካተተው የሕክምና ቡድን ወረርሽኙን መቆጣጠርና መግታት እስኪቻል ድረስ በቦታው ቆይቶ ሙያዊ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

ቡድኑ በቆይታውም ከሱዳን በመምጣት በለይቶ ማቆያ ሳይገቡ ወደ  ኅብረተሰቡ  የሚቀላቀሉ  ሰዎችን ለመለየት የቤት ለቤት ቅኝት  ሥራ የሚሰራ  መሆኑን  አስታውቀዋል።

እንዲሁም በኮሮና መከላከል ለሚሰማሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችና የጤና ባለሙያዎች ሥልጠና የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ቡድኑ የተላከው አካባቢው ከጎረቤት ሀገር በሚመጡና  ሰፊ ቁጥር  ያለው የጉልበት  ሠራተኛ  የሚሰማራባት በመሆኑ ወረርሽኙን  የመከላከል  ሥራው ውጤታማ  ለማድረግ  የበኩሉን እገዛ ለማበርከት ነው ብለዋል።

የዞኑ ኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ-ኃይል አባል  አቶ ብርሃኑ መንገሻ  እንዳሉት  የሕክምና ቡድኑ ወረርሽኙን ለመግታት እየተደረገ ያለውን ጥረት ያግዝል።

በተለይም በአካባቢው ካለው ከፍተኛ የኮሮና ወረርሽኝ ሥጋት አንጻር ይስተዋል የነበረውን የባለሙያ እጥረት የቡድኑ መምጣት በተወሰነም ቢሆን በመፍታት የተሻለ የመከላከል ሥራ ለማከናወን ያስችላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት በነበረው የቤት ለቤት አሰሳ ሥራ ቫይረሱ ያለበት ሰው ባይገኝም አሁን ሥጋቱ እየጨመረ በመምጣቱ በዞኑ እንደገና ተጠናከሮ እንዲቀጥል ይደረጋል ብለዋል።

ዞኑ ከሱዳን ጋር ባለው የድንበርና ማኅበራዊ ትሥሥር ምክንያት ለክልሉ ብሎም  ለሀገራችን ሥጋት መሆኑን ጠቅሰው ከክልሉ መንግሥት  በተጨማሪ  የፌዴራል  መንግሥት ድጋፍም እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

ድንበሩ 400 ኪሎ ሜትር የሚዋሰን በመሆኑ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞችን ለመቆጣጠር በርከት ያለ የፀጥታ አካል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም