ኮሮና ለመከላከል በሚያግዝ ድጋፍ ላይ የሁሉም ተሳትፎ እንዲጠናከር ተጠየቀ

85

ጋምቤላ፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) የኮሮና ወርርሽኝን ለመከላከል እንዲያግዝ እየተካሄደ ባለው የሀብት ማሰባሰብ ድጋፍ ላይ የሁሉም ተሳትፎ እንዲጠናከር የጋምቤላ ክልል የሀብት አሰባሰቢ ግብር ኃይል ጠየቀ።

በክልሉ ዛሬ  የምግብና ንጽሕና መጠበቂያ ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶች በድጋፍ ተገኝቷል።

የግብር ኃይሉ ሰብሳቢና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኩዋይ ጆክ ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት እንዳሉት የኮሮና ወርርሽኝ የደቀነውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመሻገር የመደጋገፉ እሴቱ ሊጠናከር ይገባል።

ወርርሽኙ እያስከተለ ያለውን ችግር መሻገር የሚቻለው ሁሉም ዜጋ እርስ በእርስ የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህሉን ማጠናከር ሲችል ነው ብለዋል።

መንግሥት ለጀመረው ወርርሽኙን የመከላከል ሥራ መሳካት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በተለይም የባለሀብቶች ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ዛሬ ድጋፍ ያደረገው ሄይኒከን ኢትየጵያ ጨምሮ ሌሎች ባለሀብቶች ላደረጉት የምግብና  ንጽሕና መጠበቂያ ስጦታ የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።

በሄይኒከን ኢትዮጵያ የደቡብ ምዕራብ ሪጅን ማስተባበሪያ የሽያጭ ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ዘሪሁን ድጋፉን ሲያስረክቡ እንደሉት ድርጅታቸው የምግብና  ንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ ያበረከተው ወርርሽኙን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ለማገዝ ነው።

በቀጣይም ከመንግሥት ጎን በመሆን በሽታውን በመከላከሉ ሥራ የበኩሉን ለመወጣት እንደሚሰራም  ገልጸዋል።

በዕለቱ በሄይኒከን ኢትዮጵያና በሞኤንኮ ጋምቤላ ቅርንጫፍ  ከ415 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላችው የምግብና ንጽሕና መጠበቂያ ሳኒታይዘር ተለግሰዋል።

በተጨማሪም የክልሉ ስድስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከዲማ ወረዳ በስጦታ የተበረከተላቸውን 36 ነጥብ 2 ግራም የወርቅ የአንገት ሀብል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ሥራ እንዲውል ለሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ዛሬ አስረክበዋል።

የሥራ ኃላፊዎች የለገሱት የወርቅ የአንገት ሀብል ሰሞኑን በዲማ ወረዳ የመስክ ጉብኝት ባካሄዱበት ወቅት ከወረዳው በስጦታ የተበረከተላቸው እንደሆነ በርክክብ መረሀ ግብሩ ላይ ተገልጿል።

በጋምቤላ ክልል እስካሁን  ከ18 ሚሊዮን 700 ሺህ ብር በላይ በጥሬ ገንዘብና የዓይነት ድጋፍ መገኘቱ ተመልክቷል።

ከዚህም ውስጥ 17 ሚሊዮን 200 ሺህ ብር  በጥሬ ገንዘብ የተገኘ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም