ፓርቲዎች የሚያስተላልፉት መልዕክት ዜጎችን ለችግር እንዳያጋልጥ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ

97

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ሆና በፖለቲካ ፓርቲዎች የሚተላለፉ መልዕክቶች ጥንቃቄ ካልተደረገባቸው ህዝቡን ላልተፈለገ ችግር ሊያጋልጥ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ድርጅት ሕብረት አሳሰበ።

በአሁኑ ወቅት በማንኛውም አካል የሚተላለፉ መረጃዎች ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩና ለሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋላጭ የሚያደርጉ እንዳይሆን ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባም ሕብረቱ ገልጿል።


የሕብረቱ ዳይሬክተር አቶ መንሱር ገበየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስና የዜጎችን ጤና ለመጠበቅ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ወቅታዊና አስፈላጊ ነው።

ይሁን እንጂ አዋጁ ክልከላ የሚያደርግባቸውን ህጎችና መመሪያዎች ቸል በማለት ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩና የሚያቃቅሩ ንግግሮችን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የሚያስተላልፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ ህብረቱ መታዘቡንም አመልክተዋል።

"ማንኛውም ዜጋ የመናገር መብት እንዳለው በሕገመንግስቱ የተደነገገ ቢሆንም አሁን አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊና አስጨናቂ ሁኔታ የሚተላለፉ ማናቸውም መልዕክቶች ጥንቃቄን ይሻሉ" ነው ያሉት።

በተለይም በህዝብ ዘንድ አለመግባባቶች እንዲፈጠሩ የሚያደርጉና በፖለቲካ ሽፋን የሚያወዛግቡ ሃሳቦችን በህዝቡ ዘንድ እንዲሰርጹ በማድረግ አላስፈላጊ ተግባር የሚፈጽሙ ፓርቲዎች ስጋት እያሳደሩ በመሆኑ ከድርጊታቸው አንዲቆጠቡ አቶ መንሱር ጠይቀዋል።

ተግባሩ ህዝቡ በኮሮናቫይረስ ላይ ማድረግ ያለበትን የመከላከልና የጥንቃቄ ተግባር የሚያዘናጋና የሚያስተጓጉል ይሆናል የሚል ስጋት በህብረቱ ላይ እንዳሳደረም ጠቁመዋል።

አቶ መንሱር እንዳሉት በተለይ ወቅቱ የኮሮናቫይረስን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ በትኩረት የሚሰራበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚሁ ተግባር ተሳትፈው ለህዝቡ ያላቸውን አለኝታነት ማሳየት አለባቸው።

ህዝቡም ሆነ አገሪቷ አሁን ባሉበት አስጨናቂ ወቅት ችግሩን የሚያባብስና መዘናጋትን የሚፈጥር ሳይሆን መፍትሄን ይዞ የሚመጣ ሃሳቦችን በማንሸራሸር ወቅቱን ለማለፍ መረባረብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

አስተያየታቸውን የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በበኩላቸው ወቅቱ መተባበርና መደጋገፍ የሚጠይቅ በመሆኑ መንግስት፣ ህዝብና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጋራ መስራት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት።

በዚህ አስከፊ ወቅት የሚተላለፉ መልዕክቶች የዜጎችን ደህንነት የሚጠብቁ፣ ህዝቡን ከኮሮናቫይረስ ስርጭት የሚታደጉና ጥንቃቄን የሚሹ ሊሆኑ ይገባል ሲሉ ፓርቲዎቹ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ቀጄላ መርዳሳ እንደገለጹት ድርጅቱ አባላቱን ከኮሮናቫይረስ እንዲጠበቁ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባር እያከናወነ ቢሆንም በቂ አይደለም።

በተለይም አባላቱ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ መሆናቸውን ተከትሎ ተንቀሳቅሶ ለማስተማርና መረጃ ለማድረስ ወቅቱ ምቹ እንዳልሆነ ነው ያስረዱት።

ይሁንና በተገኘው አጋጣሚ በተለይ በመገናኛ ብዙሃንና በማህበራዊ ሚዲያ የሚያስተላልፋቸው መረጃዎች ወቅቱን የጠበቀና የዜጎችን ደህንነት ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ኦነግም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚሁ ወቅት የሚያስተላልፉት ማናቸውም መልዕክቶች በኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ ነው አቶ ቀጄላ የተናገሩት። 

ሌላኛው የነጻነት፣ አንድነትና ፍትህ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር እንግዳወርቅ ማሞ በበኩላቸው "የተለያየ አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ችግር አንጻር አመለካከታቸውንና ፍላጎታቸውን ወደ ጎን በመተው ወረርሽኙን መከላከል ላይ በጋራ ሊሰሩ ይገባል" ብለዋል።

ከፖለቲካ ፍላጎት ይልቅ የህዝብን ጤናና ደህንነት በማስቀደም ለአገር መስራት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነትና ግዴታ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

ወረርሽኙን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁና ምርጫ መራዘሙን ፓርቲያቸው እንደሚደግፍ ገልጸው፣ ቅሬታ ያላቸው ፓርቲዎች ጥያቄያቸውን በአግባቡና ህዝብን በማያወዛግብ መልኩ ሊያነሱ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ወረርሽኙ ሁሉንም ዜጋ የሚያጠቃ መሆኑን ገልጸው፣ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ግለሰቦችም ሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች በዚህ ወቅት በሚያስተላልፉት መልእክት ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አመላክተዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት በሚደረገው ጥረትም ሁሉም አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም ነው አቶ እንግዳወርቅ የገለጹት።

ወረርኝኙን ለመግታት መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ ትክክለኛና ቀጣይነትን የሚጠይቅ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ሊቀመንበር አቶ ደረጄ በቀለ ናቸው።

ፓርቲያቸው ከጤና ሚኒስቴርና ከመንግስት ወረርሽኙን ለመከላከል በየጊዜው የሚወጡ መመሪያዎች እንዲተገበሩ በገጠራማ አካባቢ ላሉና መረጃው በሚፈለገው ልክ ለማይደርሳቸው አባላቶቹ ትምህርት እየሰጡ መሆኑን አስረድተዋል።

"ወቅቱ የፖለቲካ ጥያቄና ፍላጎት የሚንጸባረቅበት አለመሆኑን ሁሉም ፓርቲዎች ተገንዝበው ይህንን አስከፊ ጊዜ ህዝባቸውን በመታደግ ሊያሻግሩ ይገባል" ብለዋል።

በተለይም የመረጃ ክፍተት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ያሉ ዜጎች አሁንም ስለ በሽታው ያላቸው ግንዛቤ ውስን በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተንቀሳቅሰው መረጃውን ተደራሽ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አቶ ደረጄ መክረዋል።

ፓርቲያቸው በዚህ ረገድ የሚጠበቅበትን ሥራ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም ለህዝብ ያላቸውን አለኝታነት ለማሳየት የሚያደርጉት ጥረት አካል መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም