ምርምር ማዕከሉ የአፈር ለምነትን የሚመልስ ቴክኖሎጂ በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ እያላመደ ነው

64

ጎንደር፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) ጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል የማዳበሪያን ወጪ በመቀነስ የአፈር ለምነትን ለመመለስ የሚያስችል የረድፍ እርሻ ቴክኖሎጂ በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ እያላመደ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በማዕከሉ የደን ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ሲሳይ ለኢዜአ እንደተናገሩት ቴክኖሎጂው የአርሶአደሩን የማዳበሪያ ወጪ በግማሽ በመቀነስ የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ነው፡፡

በዚህም "ቴፍሮዚያ ቦጋሊ’’ የተባለውን የእጸዋት ዝርያ በአርሶአደሩ የእርሻ ማሳ በመትከል ቅጠሉ ሲያለመልም ቆርጦ በመነስነስ የአፈሩን ለምነት ለመመለስ የሚያስችል ቴክኖሎጂ መሆኑን አስረድተዋል።

የእጽዋቱ ቅጠል ፈጥኖ የመበስበስ ባህሪ ያለውና ከፍተኛ የ"ናይትሮጂን" ይዘት ያለው በመሆኑ የሰብልን እድገት በማፋጠን ሰው ሰራሽ ማዳበሪያን ለመተካት የሚያስችል መሆኑን አስታውቀዋል።

እጽዋቱ የሚተከለው በማሳው ላይ እርከን በተሰራበት ረድፍ በመሆኑ ለማረስ እንደማያስቸግርና አገልግሎቱ ካበቃ በኋላ ስሩና ግንዱን በቀላሉ የሚወገድ ነው ብለዋል።

ማዕከሉ ቴክኖሎጂውን ለመጀመሪያ ጊዜ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ በተመረጡ አስር  ሞዴል አርሶ አደሮች የእርሻ ማሳ ላይ በማላመድ ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት አስተባባሪው ከመጪው ዓመት ጀምሮ ወደ ሌሎች ወረዳዎች ለማስፋት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በቅርቡ የመስክ ጉብኝት በማዘጋጀት ቴክኖሎጂውን ለዞኑ አርሶ አደሮች ለማስተዋወቅ የታሰበ ቢሆንም አሁን ከተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር ተያይዞ ለጊዜው መዘግየቱን ጠቁመዋል።

በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የጭንጫዬ ቀበሌ አርሶ አደር እንየው መላኩ በሰጡት አስተያየት  "ቴክኖሎጂው የአፈር ለምነትን ይጨምራል፤ የማዳበሪያ ወጪንም ይቀንሳል ስላሉኝ ተክሉን በማሳዬ ላይ ማልማት ጀምሬአለሁ" ብለዋል፡፡

አሁን በአንዱ ማሳ ላይ የጀመሩት  ስራ ውጤቱን በማየት በቀጣይ በሌሎች ማሳዎቻቸው ላይ ለማስፋፋት እንደሚሰሩ አመልክተው ለሌሎች ጎረቤቶቻቸውም በማሳየት እንዲጠቀሙ  የሚያግዙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

"ምርምር ማዕከሉ የአፈር ለምነት የሚጨምር የእጽዋት ዝርያ ለሙከራ አቅርቦልኝ በማሳዬ ላይ አልምቻለሁ" ያሉት ደግሞ የዚሁ ወረዳ  አርሶአደር ውዱ ተፈራ ናቸው፡፡

ተክሉ መሬት እንደሚያዳብርና የማዳበሪያ ወጪንም እንደሚቀንስ የምርምር ማዕከሉ ባለሙያዎች ከተሰጧቸው  ምክርና ትምህርት በመረዳት ተግባራዊ እያደረጉ መሆናቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዓመታዊ የሰው ሰራሽ ማዳበሪያ አቅርቦትና ፍጆታን በተመለከተ በተያዘው የምርት ዘመን  473ሺ ኩንታል መድረሱን ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም