ኮቪድ-19 በግብርናው ዘርፍ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቋቋም እየተሰራ ነው--የኦሮሚያ መንግሥት

70

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመቋቋም እየተሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ገለጸ።

የክልሉ የግብርና ዘርፍ እንቅስቃሴ ሰሞኑን ተጎብኝቷል።

በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የክልሉ መንግሥት ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ በዚህ ወቅት  ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት  " የክልሉ  መንግሥት  በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን  በማሳደግ የአርሶ አደሩን  ህይወት  ለውጦ ኢኮኖሚውን ለመታደግ በመካናይዜሽን የተደገፈ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል''።

በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ አስጊ የሆነው የኮሮና ቫይረስ በጤና ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት ባለፈ፤ ኢኮኖሚውንም ክፉኛ ሊጎዳ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግሥትም በተለይ በገጠሩ አካባቢ ወረርሽኙን እየተከላከለ በግብርናው ዘርፍ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ  በማጠናከር ቫይረሱ በኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን  ጉዳት   ለመቀነስ እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡

የግብርናውን እንቅስቃሴ ለማዘመንና በመካናይዜሽን ለማገዝ ለአርሶ  አደሮች  ግብዓቶችን  በማሟላት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት 354 ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮቹ መከፋፈላቸውን አቶ አዲሱ አስታውሰው፣ በቅርብ ጊዜም 2ሺህ ትራክተሮችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

ወጣቱንም ወደ ግብርናው ለማስገባት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በክልሉ አርሶ አደሩን ለመደገፍ የተሰራው ስራ ከቃል የዘለለ አልነበረም ያሉት አቶ አዲሱ፣ ከፍተኛ የመንግሥት አካላትና ምሁራን በክልሉ ጉብኝት ማድረጋቸው ወደፊት ለሚዘጋጁ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ከአርሶ አደሩ ፍላጎት አንጻር ለመቃኘት  ያግዛል ብለዋል፡፡

 የክልሉ መንግሥት በአምራቹና በተጠቃሚው መካከል ሆነው የአርሶ አደሩን ልፋት ዋጋ እንዳያገኝ የሚያደርጉትን ደላሎች ለማስወጣት እየሰራ ይገኛል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ በክልሉ እየተካሄዱ የሚገኙትን የልማት እንቅስቃሴ በተለያዩ አካላት አስጎብኝቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም