በአሶሳ ኮሮናን ለመከላከል ተጨማሪ መናኸሪያና የግብይት ቦታዎች ተዘጋጁ

72

አሶሳ፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) በአሶሳ ከተማ ኮሮናን በመከላከሉ ሂደት የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት ተጨማሪ መናኸሪያና የገበያ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ።

የከተማ አስተዳዳሩ ከንቲባ አቶ ዑመር መሐመድ ለኢዜአ እንዳሉት አስተዳዳሩ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በትኩረት እየሠራ ነው፡፡

ይሁንና አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ረገድ ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ ተደጋጋሚ ትምህርት ቢሰጥም የሚፈለገውን ያክል ለውጥ አልመጣም ብለዋል፡፡

ችግሩ በተለይም በግብይት፣ በአገልግሎት መስጫ፣ በትራንስፖርትና መሰል ቦታዎች በስፋት እንደሚታይ አስረድተዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ ከፍተኛ ሕዝብ ሲያስተናግድ ከነበረው ብቸኛው የከተማ አውቶቡስ መናኸሪያ በተጨማሪ የመለስተኛ አገር አቋራጭ ጊዜያዊ መናኸሪያ ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡

የኅብረተሰቡን አሰፋፈር፣ የትራንስፖርትና ሌሎችንም መሠረታዊ አገልግሎቶችን ባማከሉ ቦታዎች ሦስት ጊዜያዊ የግብይት ሥፍራዎች ተዘጋጅተው የፊታችን ቅዳሜ ሥራ ይጀምራሉ ተብሏል።

ሁኔታዎች በዚህ መልኩ ከተመቻቹ ቀጣዩ ሥራ የአስተዳደሩ አዋጁን  በሚገባ  ማስተግበር  ነው  ያሉት አቶ ዑመር ከዚህ በኋላ በተለይም  አካላዊ ርቀትን  በማይጠብቁ  ሰዎች ላይ  ተገቢው እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

በከተማው ብቸኛ በሆነው የቅዳሜ ገበያ ቦታ ላይ የሰው መጠጋጋት ከሚገባው በላይ ቸልተኝነት ይታይበታል ያሉት የአሶሳ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ዘይነባ ዓለም ናቸው።

አስተዳደሩ የወሰደው እርምጃ አካላዊ ርቀታችንን በመጠበቅ ከቫይረሱ ራሳችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል ብለዋል፡፡

አሶሳ ከተማ 100 ሺህ የሚጠጋ ሕዝብ እንደሚኖርባት ከአስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም