በኢትዮ-ጅቡቲ ድንበር አቅራቢያ የድንበር ተሻጋሪ ተሽከርካሪዎች መናሃሪያ ሊገነባ ነው

42

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) በኢትዮ-ጅቡቲ ድንበር አቅራቢያ የድንበር ተሻጋሪ ተሽከርካሪዎች ማቆሚያ (መናሀሪያ) ሊገነባ ነው።

በሶማሌ ክልል አይሻ ደወሌ ወረዳ 01 ቀበሌ የተመረጠው ይህ ስፍራ 6 ሄክታር ስፋት ባለው ቦታ የሚገነባ ነው ተብሏል።

የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ  ያደታ እንዲሁም ሌሎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ከክልሉ መንግስት የተሰጠው የመስሪያ ቦታ ርክክብ ተፈፅሟል።

ከጅቡቲ ወደብ 120 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው አይሻ ደወሌ የተሽከርካሪዎች ማቆሚያ (መናሀሪያ) ግንባታው ሲጠናቀቅ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እንደሚፈታ ይጠበቃል።

ማዕከሉ በአሽከርካሪዎች ላይ የሚፈጠረውን እንግልት በማስቀረት ስራቸውን በተረጋጋ መልኩ እንዲያከናውኑ በማድረግ አጋዥ እንደሚሆንም ተመልክቷል።

አካባቢው ወደ ከተማነት እንዲያድግና እንዲለማ፣ ለወጣቶች የስራ ዕድል እንዲፈጠርና አካባቢያዊ ልማትም ላቅ ያለ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል።

ማዕከሉ በተለይም ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ኮቪድ 19ን ለመከላከል ሲባል ቀሪ ጥናቶች በአስቸኳይ ተጠናቀው ወደ ግንባታ እንዲገባ ይደረጋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም