ዘንድሮ የሚከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዝግጅት ተጠናቋል

120

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) በዚህ ዓመት የሚከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ቅድመ ዝግጅቱ ማጠናቀቁን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጉለሌ እፅዋት ማእከልም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለተከላ ዝግጁ ማድረጉን ገልጿል።

በ2011 ዓ.ም የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ''አረንጓዴ አሻራ ማሳረፍ" በሚል መሪ ሃሳብ በብሄራዊ ደረጃ ከ4 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸው የሚታወስ ነው።

በዘንድሮው ዓመትም ይህንኑ በጎ ጅምር በማሳደግ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተለያዩ ዝግጅቶች በመደረግ ላይ ናቸው።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፈው ዓመት የነበረውን ተሞክሮ በመቀመር ዘንድሮ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ እየተሰራ ነው።

በአሁኑ ወቀት ችግኞቹ የሚተከሉባቸው ቦታዎች በዘመናዊ ዳታ ቤዝ እንዲገቡ እየተደረገ ሲሆን በየአካባቢው የሚተከሉባቸው የጊዜ ሰሌዳም /ካሌንደር/ ተዘጋጅቷል ብለዋል።

በችግኝ ተከላ መርሃ ገብሩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞት መትከል መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ነባርና ሀገር በቀል ችግኞችም እንደሚተከሉ ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ሳኒ ገለፃ ለችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ከችግኝ ማፍላት ጀምሮ ሌሎች አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቀዋል።

በተለይም እንደ ሀገር የአፈር ለምነትን የሚያሻሽሉ፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው፣ አግሮ ኢኮሎጅው ላይ ለውጥ የሚያመጡ ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ነው ያብራሩት።

ለዚህ እቅድ ስኬትም ክልሎች አሁን ባለው የግንኙነት አማራጭ ተጠቅመው ሕብረተሰቡን የማዘጋጀት ስራ እያከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ከ6 ሺህ 500 እስከ 7 ሺህ የሚደርሱ የእፅዋት ዝርያዎች ሲገኙ ከነዚህ መካከልም 10 በመቶው ብርቅዬዎች መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የጉለሌ እጽዋት ማእከል ምክትል ዳይሬክተር አቶ አበበ ተቀባ እንዳሉት በዘንድሮው ዓመት የሚተከሉ ችግኞች ሀገራዊ እንዲሆኑና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲኖራቸው ለማድረግ ማእከሉ አስቀድሞ ከተለያዩ አካላት ጋር እየሰራ ነው።

ማእከሉ በፍጥነት ለተከላ የሚደርሱ 100 የእጽዋት ዝርያዎችን በማፍላት 550 ሺህ ችግኞችን ለተከላ ዝግጁ ማድረጉንም ገልጸዋል።

"ችግኞችን መትከል ብቻ ለታለመለት አላማ አንዲውሉ አያደርግም" ያሉት አቶ አበበ አምና ከነበረው ልምድ በመነሳት ችግኞች ከተተከሉ በኋላ ተመልሶ ለመንከባከብ ያለው ተነሳሽነት ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም እንደ ሀገር የተዘጋጁት ችግኞች ለታለመለት አላማ እንዲውሉ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይገባዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም