በሀዋሳ ከተማ ከለጋሾች በየወሩ ከአንድ ሺህ 200 ዩኒት በላይ ደም እየተሰበሰበ ነው

52

ሀዋሳ፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) በሀዋሳ ከተማ በበጎ ፈቃደኝነት ደም ከሚለግሱ ሰዎች በየወሩ ከአንድ ሺህ 200 ዩኒት በላይ እየሰበሰበ መሆኑን የከተማው ደም ባንክ አገልግሎት ገለጸ።

የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ  ደም ልገሳ ትኩረት በመነፈጉ ከፍተኛ የሆነ የደም እጥረት አጋጥሞ እንደነበር ተመልክቷል።

የደም ባንኩ አገልግሎት ተወካይ አቶ ደምስስ ሽርበዛ ለኢዜአ እንደገለጹት  በጋጠመው እጥረት ምክንያት በህክምናውና  ደም በሚፈልጉ  ታካሚዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮ ቆይቷል።

ችግሩን ለማቃለል ለቀረበው ጥያቄ  የሀዋሳ ከተማ  ነዋሪዎች  ባደረጉት ቀና ምላሽ ባንኩ በየወሩ ከ1 ሺህ 200 ዩኒት በላይ ደም መሰብሰብ  መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በደም ልገሳ ረገድ ህብረተሰቡ እያሳየ ያለው መነቃቃት በደም አቅርቦት ላይ አጋጥሞ የነበረው ችግር እየተፈታ መሆኑን ገልጸዋል።

ባንኩ ከበጎ ፈቃደኞች የሚሰበስበውን ደም ለሀዋሳና አካባቢዋ ለሚገኙ አጎራባች ዞኖችን ጨምሮ  ከ40 በላይ ጤና ተቋማት ተደራሽ እንደሚያደርግ ያመለከቱን አቶ ደምስስ ማህበረሰቡ የጀመረውን ደም የመለገስ ተግባር  አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

ደም ሲለግሱ ከነበሩት መካከል በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ መርዕድ በሰጡት አስተያየት በደም እጥረት ህይወታቸውን የሚያጡ ዜጎችን ለመታደግ በመነሳሳት መለገሳቸውን ተናግረዋል።

በእሳቸው የደም ልገሳ   ሌሎች ሲድኑ ማየት የሚሰጠው የአዕምሮ እርካታ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው  ማንኛውም ጤናማ የሆነ ሰው የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በደም እጥረት  የተቸገሩ ወገኖች እንዳሉ በመገናኛ ብዙሃን በመስማታቸው በደም ልገሳው ላይ መሳተፋቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛዋ የከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ማስረሻ ጉልላት ናቸው።

ደም መለገስ በግለሰቡ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያስከትል ከጤና ባለሙያዎች እንደተረዱ አመልክተው "ካልሰጠነው በራሱ እየሞተ የሚሄድ ስለሆነ እየተቸገሩ ያሉ ወገኖችን መርዳት ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ነው "ብለዋል።

ለመጀመሪያ ዙር ደም መለገሱን የተናገረው  ወጣት ታሪኩ መኮንን በበኩሉ በወረርሽኝ ምክንያት የተፈጠረውን የደም እጥረት ለማቃለል ድጋፍ በማድረጉ መደሰቱን ተናግሯል።

"በምንችለው መደጋገፍ ተገቢ ከመሆኑም  ባለፈ ለወገን ደራሽ ወገን ነውና ሁሉም ዜጋ በመርሃ ግብሩ የራሱን አስተዋጽኦ ቢያደረግ መልካም   ነው " ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

በሀዋሳ ከተማ  በበጀት ዓመቱ  ለመሰብሰብ ከታቀደው የደም  መጠን ውስጥ እስካሁን 90 በመቶው ማከናወን እንደተቻለ ከደም ባንክ አገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም