የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር አብራሃም በላይ ለግንቦት 20 በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ

146

ትግራይ፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር አብራሃም በላይ የግንቦት 20 በዓልን በማስመልከት መልእክት አስተላለፉ።

በመልእክታቸውም የአሁኑ ትውልድ ትግል በጠነከረ ህብረ ብሔራዊ ተጋድሎ ወደ አዲስ አውድ እንደሚሸጋገር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የአገራችን ሕዝቦች በትውልድ ቅብብሎሽ በታሪክ ካጋጠሟቸው የሉአላዊነት አደጋዎችና ዘርፈ ብዙ ፓለቲካዊ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በህይወት መስዋእትነትም ጭምር በተከፈለ ውድ ዋጋ አልፈው የዛሬይቱን ኢትዮጵያ አስረክበውን በክብር አልፈዋል።

ሀገራችን በዘመናት ሒደት ያጋጠሟት እነዚህ ልዩ ልዩ ፈተናዎች ለእያንዳንዱ ትውልድ ልዩ የዚያ ዘመንና ትውልድ ታሪካዊ ተልዕኮዎችና የቤት ስራዎች መሆናቸውን ስንገነዘብም የአሁኑ ትውልድ ዘመኑን መርምሮና ዋጅቶ ሊፈፅማቸው ስለሚገቡ ዘመን ተሻጋሪ የታሪክ ተልእኮዎቹ ቆም ብሎ ሊጠይቅና ሊያስተውል እንደሚገባው በመገንዘብ ነው።

የግንቦት 20 በዓል አከባበር ፋይዳና ተምሳሌትነትም በአብዛኛው በታሪክ በተለምዶ የ60 እና የ70ዎቹ ትውልድ ተብሎ የሚታወቀው ትውልድ በሕዝቦች ላይ ይደርስ የነበረውን የመብት ረገጣ ጭቆና ግፍና አፈና ለመቀልበስ ዘመኑ የሰጣቸውን ታሪካዊ ተልዕኮ በመስዋእትነት በመወጣት የፈፀሙትን ታሪካዊ ገድል በክብር የምንዘክርበትና የመስዋእትነቱንም ፍሬ ለሕዝቦች መብት መከበርና ጥቅም መረጋገጥ ባስገኘው ተጨባጭ ውጤት ላይ እውነተኛ የህሊና ዳኝነት እየሰጠን ሊሆን ይገባል ብሏል ፓርቲው በመግለጫው።

ይህ ትውልድም በዚህ ዘመን ልዩ የሆነ የታሪክ ተልዕኮ ያለው ሲሆን ከፊቱም በርካታና ውስብስብ ችግሮች ተደቅነውበት ይገኛሉ።

በተለይም ሁለንተናዊ ቀውስ በዓለማችን ብሎም በሀገራችን በማስከተል የሚገኘውና በፍጥነት በመዛመት ላይ ያለው የኮሮናቫይረስ ወረርሸኝ ትልቅ የአደጋ ስጋት መሆኑን ጠቅሷል።

በሽታው በሀገራችን ከተከሰተበት ግዜ ጀምሮ በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የተደገፋ ልዩ ልዩ የመከላከልና ስርጭቱን የመቆጣጠር እርምጃዎች በመንግስት በኩል ቢወስዱም አጥጋቢ ውጤት ባለመገኘቱ ሌሎች ጠንከር ያሉ እርምጃዎች መውሰድ የምንገደድበት ሁኔታ ውስጥ እንደምንገኝ መንግስት ይፋ አድርጓል።

ይህ የህልውና ስጋት የሆነብን ችግርም ከምንግዜውም በላይ የበለጠ መረዳዳትና የጋራ አቋም የሚፈልግ ሲሆን በመንግስት በኩል ከሚወሰዱ እርምጃዎች በተጨማሪ ህብረተሰቡ ግንዛቤውን በማጥራት በመንግስትና ሌሎች የተረጋገጡ ምንጮች የወረርሽኙን ስርጭት ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚሰጡ የጥንቃቄ ምክሮችን ማድመጥና ያለመታከት መተግበር ይመከራል።

ይህ ትውልድ በሌላ ግንባር ከከፈታቸው የጥቃት ርምጃዎች አንዱና ዋነኛው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክታችን ግንባር ቀደም ተጠቃሹ ነው።

በዚህ የትግል አውድም ሕዝባችን ከጅማሬው አንስቶ ለፕሮጀክቱ የከፈለውና በመክፈል ላይ የሚገኘው መስዋእትነትም በታሪከ በመጪው ትውልድ የሚወሳ ነው።

የግድባችን ጉዳይ በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰነዘሩ ግልፅና ስውር ትንኮሳዎች ቢኖሩበትም ህዝብና መንግስታችን ህግና ፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማያረጋግጡ ድምፆች ጆሮ ሳይሰጥና ሳይዘናጋ በመሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሀቅ በተግባር ለመቀየር የመጨረሻው ምእራፍ ላይ ይገኛል።

በዚህ አጋጣሚ መላው ሕዝባችን ይህንን ጉዳይ በልዩ ትኩረት እንዲከታተለውና በሀገር ብሔራዊ ጥቅም ላይ እጃቸውን ለማስገባት ለሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን አጥብቆ እንዲኮንን በማለት ዶክተር አብራሃም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ይህ ትውልድ በዘመኑ የተጋረጡበትን ጉልህ አደጋዎች በፍፁም ህብረ ብሄራዊነት ለመመከት ከምንግዜውም በላይ አንድነቱን አንዲጠብቅና የነገይቱን ሰላማዊት አለማችና በአንድነቷ የጠነከረች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ አበክሮ በመስራት የድል ብስራቱን ወደ አዲሰ አውድ እንዲያሸጋግር አሁንም የአደራ መልእክቴን አስተላልፋለሁ ብለዋል።

በመጨረሻም የግንቦት 20 በዓልንና የበዓሉን ትርጉም በማጣጣም ሕዝባችን ዘመን ተሻጋሪ ደማቅ ታሪክ በድጋሚ እንደሚፅፍ ያለኝን ጠንካራ እምነት ስገልፅ በዓሉ የደስታና የሰላም እንዲሆንልን ከልቤ በመመኘትም ጭምር ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም