“ግንቦት 20 ለሶማሌ ክልል ህዝብ ካስገኘለት ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል”... አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ

62

ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) ግንቦት 20 ለሶማሌ ክልል ህዝብ በቋንቋው ከመማርና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ካስገኘለት ጥቅም ይልቅ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የፀጥታ ችግር በመፍጠር መጥፎ አሻራ ማሳረፉን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ገለፁ፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ግንቦት 20 በአገር አቀፍ ደረጃ የፌዴራል ሥርዓት ተግባራዊ በመደረጉ የሱማሌ ክልል ህዝብ በቋንቋው የመማር፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ያገኘበት ቢሆንም የክልሉ ህዝብ ካገኘው ጥቅም ይልቅ በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በውሸት ፌዴራሊዝምና እና በሀብት ዘረፋ ከደረሰበት የከፋ በደል የተነሳ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡

በግንቦት 20 ምክንያት በአገር አቀፍ ደረጃ በመጡ አንዳንድ ለውጦች የሱማሌ ክልል ሕዝብ የተጠቀመበት መሆኑን አውስተው፤ በሕውሓት የተመራው ሥርዓት በሶማሌ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መጥፎ አሻራ በማሳረፉ ሥርዓቱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ሕወሓት የሚመራው ሥርዓት በአገር አቀፍ ደረጃ ሲያራምድ የነበረው ህዝብን ከህዝብ የማጋጨትና የጥላቻ ፖለቲካ እንደነበር አመልክተው “ሥርዓቱ በሱማሌ ህዝብ ላይ በታሪኩ ተፈፅሞበት የማያውቀው ግፍ፣ ግድያ፣ ማንገላታት አድርሶበታል፤ በተደራጀ መልኩ ህባችንን የማዋረድ ሥራ ተሠርቷል” ብለዋል ።

“የሶማሌ ክልል አሁን ባለው ለውጥ ደስተኛ ነው” ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ በኮንትሮባዲስቶችና በእነሱ ኔት ወርኮችና ተጠቃሚዎች አማካኝነት የሚሞከሩ አፍራሽ ሥራዎች ቢኖሩም የክልሉ ተቋማት በተካሄዱት የሪፎርም ሥራዎች ጠንካራ በመሆናቸው፤ ችግሮቹን አስተማማኝ በሆነ መልኩ መመከት የሚያስችል አቅም መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

በለውጡ ወቅት የተሰሩት የልማት ሥራዎች በ27 ዓመታት ከተሠሩ ሥራዎች እንደሚበልጡ ገልጸው ፤ በክልሉ ቀደም ሲል በአምስት ዓመት ሰባት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲሰሩ፤ ከለውጡ በኋላ ባለው አንድ ዓመት ከመንፈቅ በሚሆን ጊዜ 50 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን ለአብነትም ጠቅሰዋል።

ክልሉ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እያካሄደ እንደሚገኘ ገልፀው፤ በጎዴ፣ በቀብሪ ደሃርና በደገሐቡር ከተሞች በሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው ብለዋል።

በመንገድ ልማትም አንድ ሺ 11 ኪሎ ሜትር የገጠርና 24 ኪሎ ሜትር የከተሞች አስፓልት የመንገድ ግንባታዎች እየተካሄዱ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ ለ 200 ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው መሆኑንና ከእነዚህ መካከል 35 ሺዎቹ በክልሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መቀጠራቸውን ገልጸዋል።

የሚካሄዱ ፈርጀ ብዙ የልማት ሥራዎች የሱማሌ ክልል ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን ያመለከተቱት አቶ ሙስጠፌ፤ በአገርም ሆነ በክልሎች ደረጃ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።

ማንኛውም ሥርዓት ጠንካራና ደካማ ጎን እንዳለው በመጥቀስ ደካማውን በማረም ጥንካሬውን ማስቀጠል እንደሚገባም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም