አየር መንገዱ የኢንዱስትሪ ፓርክ ምርቶችን በስፋት እያጓጓዘ መሆኑን አስታወቀ

64

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ አበባን ጨምሮ የኢንዱስትሪ ፓርክ ምርቶችን በካርጎ ጭነት ወደ ውጭ ገበያ እያጓጓዘ መሆኑን አስታወቀ።

በዓለም አገራት የተስፋፋው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሰዎች ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ መገደቡን ተከትሎ በርካታ አየር መንገዶች እንቅስቃሴያቸውን በማቆም ሠራተኞቻቸውን አያሰናበቱ ይገኛሉ።

ሌሎችም አየር መንገዶች ከመንግስታቸው ከፍተኛ የሆነ ድጎማ እየጠየቁ መሆኑ እየተገለጸ ይገኛል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን በአሁኑ ወቅት የወረርሽኙን ተጽዕኖ ለመቋቋም በመንገደኞች ያጣውን ገቢ ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም በተወሰነ ደረጃ ለማግኘት ፊቱን ወደ ካርጎ አገልግሎት አዙሯል።

በዚህም በርካታ የሰብዓዊ እና ሌሎች የነፍስ አድን ድጋፎችን ለአህጉሪቷ፣ አፍሪካና ሌሎች የዓለም ክፍሎች እያደረሰ ይገኛል።

በተጨማሪም አየር መንገዱ ይህን ክፉ አጋጣሚ ወደ መልካም በመቀየር የካርጎ አገልግሎቱን ለኢንዱስትሪ ፓርክ ላኪ ድርጅቶች የዋጋ ቅናሽ በማድረግ የአበባና ሌሎች ምርቶችን ወደ ውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ እስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በገጠመው ተግዳሮት ሳይበገር ሌሎች አማራጮችን ተጠቅሞ እየሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በካርጎ አገልግሎቱ የሚሰጡ የሰብዓዊ ድጋፎችን ከማጓጓዝ ጎን ለጎን አበባን ጨምሮ በርካታ ምርቶችን ወደ ውጭ በማጓጓዝ ገበያ የማፈላለግ ሥራም እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በአፍሪካ ቁጥር አንድ የአበባ አምራችና ላኪ የነበረችው ኬንያ ትጠቀም የነበረው የአውሮፓ አየር መንገዶችን እንደነበረና በአሁኑ ወቅት ሥራ በማቆማቸው በአገሪቱ ያሉ ላኪዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድን የመጠቀም ፍላጎት ማሳየታቸውን ተናግረዋል።

"በኢኮኖሚው መስክ ለመደጋገፍ ሲባል በኢትዮጵያ ለሚገኙት ላኪዎች ቅድሚያ በመስጠት እየሰራን ነው" ያሉት አቶ ተወልደ፣ የአበባ ምርት ብቻ በቀን ከ200 ቶን በላይ ኤክስፖርት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የሥጋ ኤክስፖርትን በተመለከተ የረመዳን የጾም ወቅትን ተከትሎ ወደ መካከለኛው ምስራቅ በርካታ ምርት መላኩንም  አስረድተዋል።

አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም ከካርጎ አገልግሎት 15 በመቶ፤ ከመንገደኞች ደግሞ 85 በመቶ ገቢ ያገኝ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ከመንገደኞች የሚገኘው ገቢ በመቆሙ የካርጎ አገልግሎቱ ወደ 30 በመቶ ማደጉ ተገልጿል።

"የካርጎ አገልግሎት ገቢው የበፊቱን ገቢ ሙሉ ለሙሉ ባይተካ እንኳ ድርጅቱ የገጠመውን ችግር ተቋቁሞ የሠራተኞችን ደመወዝና ሌሎች ወጪዎችን ለመሸፈን እንዲሁም የአውሮፕላኖቹን እዳ ለመክፈል ያስችላል" ነው ያሉት ዋና ሥራ እስፈጻሚው።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ እስፈጻሚ ወይዘሮ ሌሊሴ ነሚ በበኩላቸው፣ የኢንቨስተሮች የምርት እንቅስቃሴ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን ተናግረዋል።

"ይህንን ለመደገፍና አምራቾች ወደ ሥራ እንዲገቡ በአየር መንገዱ በኩል እስከ ስድስት ወር የሚቆይ የማጓጓዣ ቅናሽ መደረጉ ትልቅ ማበረታቻ ነው" ብለዋል።

አየር መንገዱ ለሚሰጠው የካርጎ ጭነት አገልግሎት በቀን 50 በረራዎችን እያደረገ ነው።

ከዚህ በተጓዳኝ በጃክማ ፋውንዴሽን በተለያዩ ጊዜያት የተለገሱትን የኮሮናቫይረስ ቅድመ መከላከያ መሳሪያዎችን እንዲሁም ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎችን ወደ 54ቱ የአፍሪካ አገራት ማጓጓዙ ይታወሳል።

ከዚህ ቀደም 12 የካርጎ ጭነት አገልግሎት የሚሰጡ  የነበሩ አውሮፕላኖች  አየር መንገዱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ 25 የመንገደኛ አውሮፕላኖችን ወደ ካርጎ አገልግሎት በመቀየር ለ24 ሰዓት እየሰራ  መሆኑንም አስታውቋል።

አየር መንገዱ የካርጎ አገልግሎቱን ለማስፋትና ለማዘመንም 150 ሚሊዮን ዩሮ እንደወሰደበት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም