በአሜሪካ በኮቪድ19 ቫይረስ የሟቾች ቁጥር ከ100 ሺህ አለፈ

76

አዲስ አበባ፣ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ 'ቀላል ጉንፋን ነው' ሲሉ ያጣጣሉት ቫይረስ የመቶ ሺህ ዜጎቻቸውን ሕይወት ቀጠፈ።

አሜሪካ በኮሮናቫይረስ የሞቱባት ዜጎች ቁጥር ባለፉት 44 ዓመታት በቬትናም፣ በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታንና በኮሪያ ጦርነቶች የሞቱባት ዜጎች ተደምረው እንኳ የሚበልጥ መሆኑን የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል፡፡

የመጀመርያው በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው በአሜሪካ የተገኘው በጥር 21 ነበር፡፡

አሐዞችን እየተከታተለ ይፋ የሚያደርገው የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ እንደሚያስረዳው አሁን በትክክል በአሜሪካ ምድር የተመዘገበው የሟቾች ቁጥር 100 ሺህ 276 ነው፡፡

ከማዕከሉ የተገኘው አሀዝ እንደሚያሳየው አብዛኛዎቹ ሟቾች ዕድሜያቸው ከ85 ዓመት በላይ የሆኑ ናቸው።

ትራምፕም ሆነ ሌሎች ፖለቲከኞች ወረርሽኙ በዚህ አጭር ጊዜ እንዲህ አሜሪካንን የሚያህል አገር በእምብርክክ ያስኬዳል ያለ አልነበረም ሲል ዘገባው አመልክቷል፡፡

አሜሪካንን ኮቪድ19 በአራት ወራት ውስጥ አንድ ሚሊዮን ሰባት መቶ ሺህ ዜጎቿን ሰቅዞ ይዞ፣ አንድ መቶ ሺዎቹን ደግሞ ከዚህ ዓለም በሞት አሰናብቷል፡፡

በዓለም ላይ በኮቪድ19 ቫይረስ ከተያዘው ሰው 30 ከመቶው አሜሪካዊ በመሆኑ በዓለም 9ኛዋ ተጠቂ አገር አድርጓታል፡፡

በመላው ዓለም በቫይረሱ የተያዙት ቁጥር ከ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሲያሻቅብ የሟቾች ቁጥር ደግሞ 354 ሺህ 984 ደርሷል፡፡

የአሜሪካው የበሽታ መቆጣጠር ና መከላከያ ማዕከል-ሲዲሲ በአገሪቱ በቫይረሱ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥርን በዕድሜ ከፋፍሎ አስቀምጧል።

ኒው ዮርክ፣ ኒው ጀርሲ እና ማሳቹሴት ግዛቶች ደግሞ በርካታ ሰዎች የሞቱባቸው ቀዳሚ የአሜሪካ ግዛቶች ናቸው።

እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አሀዝ መሠረት፤ በብራዚል 15 በመቶ የኮቪድ-19 ሟቾች ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በታች የሆኑ ናቸው።

በሜክሲኮ ደግሞ 25 በመቶ የሚሆኑት ከ25 እስከ 49 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ቢቢሲ በዘገባው አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም