ኢትዮጵያ የጤና ስጋቶችንና አደጋዎችን የብሔራዊ ደህንነት ምላሽ ስርአት ውስጥ ማካተት አለባት ተባለ

85

አዲስ አበባ ግንቦት 19/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የጤና ስጋቶችንና አደጋዎችን የብሔራዊ ደህንነት ምላሽ ስርአት ውስጥ ማካተት እንደሚገባት ተገለጸ። 

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር 'የኮቪድ-19 በዓለም አቀፍና አገራዊ ደህንነት ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ' በሚል ርዕስ ያዘጋጀው በኢንተርኔት የታገዘ ጉባኤ (ዌቢናር) ዛሬ ተካሂዷል።

በሁለት ምሁራን ለውይይት መነሻ የሚሆኑ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበዋል።

የህክምና ተመራማሪና አማካሪ ዶክተር ጌትነት ይመር የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19)ን ጨምሮ ሌሎች ወረርሽኞች የሚያደርሱት ጉዳት መጠነ ሰፊና ብዙ ገጽታ ያለው እንደሆነ ገልጸዋል።

በተለያየ ጊዜ በነበሩ ታሪካዊ ኩነቶች ከጦርነቶች ይልቅ ወረርሽኞች የሚያደርሱት ዘርፈ ብዙ ጉዳት የከፋ የነበሩባቸው አጋጣሚዎች እንደነበሩ አውስተዋል።

ዓለም ወደ አንድ በመጣችበት በአሁኑ ወቅት ወረርሽኞችና በአጠቃላይ የጤና ስጋቶች ከጤና ባለፈ በብሔራዊ ደህንነት ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳድሩ አመልክተዋል።

''በዓለም አቀፍ ደረጃ የጤና ስጋቶችን እንደ ብሔራዊ ደህንነት የማየት ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል'' ብለዋል።

አገሮች በአሁኑ ሰአት በተለያየ ጊዜ የጤና ስጋት የሚሆኑ ወረርሽኞችና በሽታዎች ሲገጥሟቸው እንደ ብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ በማየት ምላሽ እየሰጡ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያም የጤና ስጋቶችንና አደጋዎችን የብሔራዊ ደህንነት ምላሽ ስርአት ውስጥ ማካተት እንደሚገባት ነው ዶክተር ጌትነት ያመለከቱት።

'ጤና ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ወረርሽኞችን ለመከላከል የሚያስችል የጤና ደህንነት ተቋም ሊኖራት ይገባል'' ብለዋል።

አገሪቱ የብሔራዊ ደህንነትን አስመልክቶ ባሏት ሰነዶች ውስጥ የጤና ስጋቶችንና አደጋዎችን የማካተት ጉዳይ በቀጣይ ተከታታይ የሆነ ውይይትና ምክክር እንደሚያስፈልገውም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ስጋቶችንና አደጋዎችን ለመከላከል፣ አስቀድሞ ለመለየትና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም ማጠናከር እንዳለባትም ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ በበኩላቸው ''የሽብርተኛና ጽንፈኛ ቡድኖች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን እንደ አጋጣሚ ተጠቅመው ጥቃት ሊያደርሱ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል'' ብለዋል።

በኢትዮጵያም ሆነ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና በሰላምና ደህንነት ላይ የመጡ ለውጦች አደጋ ውስጥ እንዳይወድቁ ተገቢው ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።

ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ብሔራዊ የደህንነት ስጋቶች ተለይተው ሊሰራባቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አገሪቱ የብሔራዊ ደህንነት ፈተናዎች በሚገጥሟት ወቅት ብሔራዊ የጋራ መግባባት በመፍጠር መፍትሔ ማበጀት እንደሚኖርባትም አክለዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ''የውይይት መድረኩ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በደህነት ላይ የሚኖረውን አስመለክቶ ስለሚኖረው ጉዳት ጥሩ ግብአት የተገኘበት ነው'' ብለዋል።

በተነሱት ሀሳቦች ላይ በቀጣይ ጥልቅና ዝርዝር ጥናቶችን ማድረግ እንደሚገባ ያመላከተ እንደሆነም ገልጸዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያዘጋጀው ዌቢናር በየሳምንቱ ኮቪድ-19 አስመልክቶ በተቋሙ የሚካሄዱ ሳምንታዊ ውይይቶች አካል ነው።

የዛሬው ስድስተኛ የምሁራን የውይይይት መድረክ መሆኑ ይታወቃል።

ዌቢናሩ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያደርሳቸው ተጽእኖዎችና የፈጠራቸው መልካም አጋጣሚዎች ላይ ሳይንሳዊ ትንተና በመስጠት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ለሚሰሩ ስራዎች ለግብአትነት የሚውልበት መድረክ እንደሆነ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም