በሀዋሳ ከተማ ከነገ ጀምሮ የአዋጁ አስገዳጅ መመሪያዎች ተግባራዊ ሊደረግ ነው

72

ግንቦት 19/2012 (ሀዋሳ ኢዜአ) በሀዋሳ ከተማ ከነገ ጀምሮ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የተቀመጡ ጭንብል የመጠቀምና ርቀትን የመጠበቅ መመሪያዎች በአስገዳጅነት ተግባራዊ እንደሚደረጉ የከተማው አስተዳደር ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ። 

የግብረ ኃይሉ አባልና የአስተዳደር  ጤና መምሪያው ኃላፊ አቶ ቡሪሶ ቡላሾ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችል ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ  ሲሰራ ቆይቷል።

ትምህርቱ የተሰጠው በተለይ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለውን መዘናጋት ለመቀነስ ከኃይማኖት መሪዎች ፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎችም አካላት ጋር በመሆን ህዝብ በሚሰበስብባቸው ሥፍራዎች ነው።

በተጓዳኝም  ለይቶ ማቆያና ማከሚያ ማዕከላትን የማዘጋጀት ሥራም ተከናውናል ብለዋል።

በሀዋሳ እስካሁን በቫይረሱ የተያዘ ባይገኝም የቱሪስት መዳረሻ ብሎም በከተማዋ የኢንዱስትሪ ፓርክ በመኖሩ የተነሳ  የቫይረሱ ስርጭት ስጋት እንዳለ   አቶ ቡሪሶ አውስተዋል።

በመግቢያና መውጫ በሮች ላይ ከሚደረግ የሙቀት ልኬት በተጨማሪ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት የምርመራ ሥራዎች እየተከናወነ ነው።

እስካሁንም 240 ናሙናዎች ተወስደው ምርመራ መደረጉን ጠቁመዋል።

ይህም ሆኖም   መዘናጋቱ አሁንም በመኖሩ እያሰጋ የመጣውን የወረርሽኙ አደጋ ለመመከት  በከተማዋ ከነገ ጀምሮ ጭንብል የመጠቀምና ሌሎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀመጡ መመሪያዎች በአስገዳጅነት ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢና የአስተዳደሩ  ዐቃቤ ህግ መምሪያ ኃላፊ  አቶ አበዙ አስፋው በበኩላቸው ግብረኃይሉ በአዋጁ የተቀመጡ መመሪያዎችን ለማስፈፀም ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል ።

ጫፍ የወጡ አዋጁን የመጣስ ተግባራት ባጋጠሙበት ወቅት የቅጣት እርምጃዎችም መወሰዳቸውንም አውስተዋል።

እስካሁን ከ600 በላይ ተሸከርካሪዎች ከተፈቀደላቸው የተሳፋሪ ቁጥር በላይ በመጫናቸው ፣  ተገልጋዮቻቸው ርቀታቸውን ሳይተብቁ የሚያስተናግዱ ሆቴሎች ፣  ማሳጅ ቤቶች ፣ የጫትና ሺሻ ቤቶች የቅጣት ውሳኔ እንደተላለፋቸባቸውም ጠቅሰዋል።

ክልከላ የተደረገባቸው ድርጊቶችን ጥሰው የሚፈፅሙ አካላት ላይ ጠንካራ እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል።

በትራንስፖርት አገልግሎት ፣ ገበያና ሌሎች ህዝብ በሚበዛባቸው ስፍራዎች  የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ሳይጠቀሙ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም