የፀረ-ቫይረስ ሕክምና አገልግሎትን የሚያቀላጥፍ መመሪያ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
የፀረ-ቫይረስ ሕክምና አገልግሎትን የሚያቀላጥፍ መመሪያ ተዘጋጀ
አዲስ አበባ ግንቦት 19/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በሚካሄደው የኮሮና ቫይረስ መከላከል ሥራ የፀረ-ቫይረስ ሕክምና አገልግሎትን ማቀላጠፍ የሚያስችል የመሸጋገሪያ መመሪያ ተዘጋጀ።
መመሪያውን ያዘጋጀው የፌዴራል ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ/ መከላከልና መቆጣጠር ጽህፈት ቤት አዳዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች እንዳይኖሩ እየሰራሁ ነው ብሏል።
የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጽጌሬዳ ክፍሌ ለኢዜአ እንደተናገሩት ኮቪድ-19ን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት በሌሎች ዘርፎች ላይ ጫና አሳድሯል።
ከእነዚህም መካከል የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ መከላከል መርሃ ግብርን ጠቅሰው ጫናውን ለማቅለል ትኩረት መሰጠቱን አክለዋል።
የፀረ-ቫይረስ ሕክምና አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ እንዳይስተጓጎል የሚያግዝ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የተለያዩ ሥራዎች አየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ግብረ ኃይሉ የፀረ-ቫይረስ ሕክምናን በተወሰነ መልኩ ያቋረጡ ሰዎችን አድራሻ በማፈላለግ አገልግሎቱን እንዲጀምሩ ማድረጉንም ጠቅሰዋል።
ጎን ለጎንም የፀረ-ቫይረስ ሕክምና አገልግሎትን በኮሮና ቫይረስ ምላሽ ወቅት በአግባቡ መተግበር የሚያስችል የመሸጋገሪያ መመሪያ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
በመመሪያው በአጭር ጊዜ የሚሰጠውን የፀረ-ቫይረስ ሕክምና ከሦስት እስከ ስድስት ወራት ከፍ እንዲል ተደርጓል ብለዋል።
ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ሥልጠና ተሰጥቶ መመሪያውን ለመተግበር ወደ ሥራ መገባቱንም ገልጸዋል።
በተለይ በግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች የቫይረሱ ሕሙማን ሕክምናቸውን አቋርጠው ለከፋ የጤና ችግር እንዲሁም ለኮሮና ተጋላጭ እንዳይሆኑ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የኮሮናን ቫይረስ የመከላከል ሥራ በፀረ-ቫይረስ ሕክምና መረጃ አያያዝ ላይ ጫና እንዳያሳድር መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ላይ ችግሮች መስተዋላቸውን ገልጸው የተሸራረፉና ሪፖርት ያልተደረጉ መረጃዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ይህን የመረጃ አሰባሰብ ሂደት በመመሪያው ለማስተካከል እየተሰራ መሆኑንም ነው ዶክተር ጽጌረዳ የተናገሩት።
ጽህፈት ቤቱ በተጓዳኝ በኤች.አይ.ቪ/ቫይረስ/ አዲስ የሚያዙ ሰዎች እንዳይኖሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።