ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስጠበቅ የሕዳሴ ግድብን በፍጥነት መጨረስ አለብን

87

 አዲስ አበባ ግንቦት 19/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ ጥቅምና ፖለቲካን ሳናገናኝ የሕዳሴውን ግድብ ግንባታ በአንድነት መጨረስ አለብን ሲሉ የመገናኛ ብዙሃንና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ተናገሩ።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመገናኛ ብዙሃንና የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሚና በሚል በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

ባለሙያዎቹ ኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ ጥቅምና ፖለቲካን ማገናኘት የለብንም፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በአንድነት በፍጥነት መገደብን አለብን ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስጠበቅ በመቻቻልና በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ጋዜጠኛና ደራሲ ጥበቡ በለጠ የግድቡ ግንባታ ከፖለቲካ አንጻር ሊታይ አይገባም፤ ግድቡ የህልውናችን መሰረት ነው' ሲል ነው የገለጸው።

ግድቡ ከድህነት ለማላቀቅና የኃይል አቅርቦት ችግርን ከመፍታት አልፎ ከድርቅ ስጋትም የሚያወጣን ነው ብሏል።

ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ኃብት መሆኑን በመጥቀስ የፖለቲካና የእርስ በእርስ ግጭት የአገር ኢኮኖሚን የሚያቀዛቅዝ ተግባር መሆኑን ጠቁሟል።

ገጣሚ ታገል ሰይፉም መንግስት የሚከውናቸውን የልማት ስራዎች መጠራጠር አያስፈግም፣ ፖለቲካና ብሔራዊ ጥቅምንም ማገናኘት የለብንም ነው ያለው።

ከፖለቲካና ከአገራዊ ጥቅም አገርን ማስቀደም ያሻል፤ ካለፈው ስህተታችን በመማር ግድቡን በአንድነት ገንብተን ስራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል ብለዋል ባለሙያዎቹ።

አንዳንዶች ግድቡን ከፖለቲካ ጋር እንደሚያገናኙት በመጥቀስ ግድቡ የሁላችን ኃብት መሆኑን መገንዘብ ያሻል ሲሉም ገልጸዋል።

ጋዜጠኛና ደራሲ ጥበቡ በለጠ በዓባይ ወንዝ ላይ ጥናትና ምርምሮች በስፋት ሊካሄዱ እንደሚገባና ሁሉም ዜጋ ስለ ሕዳሴ ግድብ ግንዛቤ ኖሮት ማደግ እንዳለበት አመልክቷል።

በዓባይ ወንዝ ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ባለሙያዎችና የመገናኛ ብዙሃን ፕሮግራሞች ሊጠናከሩ እንደሚገባም አክሏል።

ድህነትና ኋላቀርነት ዋነኛ ጠላቶቻችን እንደሆኑ በመጠቆም የጋራ በሆኑት ጉዳዮቻችን ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል።

ገጣሚ ታገል ሰይፉ በበኩሉ ኢትዮጵያ ስለ ዓባይ በመጪው ትውልድ ላይ ልትሰራ ይገባል ይላል።

የዓባይ ወንዝ ከ75 በላይ የኢትዮጵያ ወንዞችን የውሃ መጠን ሲይዝ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ6 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት አለው፤ ከ300 ሚሊዮን በላይ ሰዎችም በአቅራቢያው ይኖራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም