በኢትዮጵያ በቀጣዩ ክረምት የድርቅ አደጋ ስጋት የለም

104

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ የ2012 ዓ.ም የክረምት ወቅት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎች የድርቅ አደጋ ስጋት እንደማይኖር የብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው የበልግ ወቅት ግምገማንና የክረምት ወቅት ትንበያ አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እንዳሉት፤ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች በቀጣዩ ክረምት በቂ እርጥበት እንደሚኖራቸው ትንበያዎች አመልክተዋል።

አካባቢዎቹ በአብዛኛው መደበኛና ከመደበኛ  በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ ጠቁመዋል።

የክረምት ወቅት የሚባለው ከመጪው ሰኔ ወር እስከ መስከረም ያለው አራት ወራት ሲሆን ይህ ወቅት በአገሪቱ  አብዛኛው የግብርና ምርት የሚመረትበት ነው።

አገር አቀፍና አለም ዓቀፍ ክስተቶችን በመዳሰስ የተሰራው ትንበያ እንደሚያመለክተው በአገሪቱ በዘንድሮ የክረምት ወቅት የድርቅ አደጋ ስጋት እንደማይኖር ነው።

በሰሜን ምዕራብና በደቡም ምዕራብ የአገሪቱ አካባቢዎች አብዛኛው መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ።

''በአገሪቱ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ከ80 በመቶ በላይ የሚበልጡ ዝናብ የሚያገኙት በዚህ ወቅት ሲሆን የትንበያው ግኝት ለግብርና ምርታማነት ከፍተኛ እገዛ እንዳለው አመላካች ነው'' ብለዋል።

የሚገኘው እርጥበት በተለይ ለመኸር እርሻ እንቅስቃሴ፣ ለአባይ ግድብ የውሃ ሙሌትና ለተፋሰሱ አካባቢዎች መልካም እድልን የሚፈጥር እንደሚሆን ገልጸዋል።

የተገኘውን መልካም እድልም የግብርና ባለሙያዎች፣ የፖሊሲ አውጪዎችና አርሶ አደሮች እንዲጠቀሙበት ጠቁመዋል።

የሚገኘው ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ደግሞ በአንዳንድ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ ስለሚያስከትል ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተለይ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች፣ በአዋሽና በአባይ ተፋሰስ እንዲሁም በባሮና አኮቦ ወንዞች አካባቢዎች ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል።

''በከተሞችም አካባቢ የጎርፍ ማስወገጃ ቱቦዎችን በማጽዳት የጎርፍ አደጋ ስጋትን መከላከል ይገባል'' ነው ያሉት።

ከዚሁ ጋር አያይዘው ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ በመጪው የበጋ ወቅት ደካማ የላሊና ክስተት ስለሚኖር የወቅቱ ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ አካባቢዎች የእርጥበት ማነስ ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል አሳስበዋል።

በአካባቢው የሚኖሩ አርብቶ አደሮች ከወዲሁ የዝናብ ጠብታን በአግባቡ መጠቀምና ማቆር እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም