በዘጠኝ ወራት ወደ ውጭ ከተላከ አጠቃላይ ምርት 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተገኝቷል

60
አዲስ አበባ ግንቦት 1/2010 በበጀት ዓመቱ በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ውጭ ከተላከ አጠቃላይ ምርት 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱን የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ። የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ፍላቴ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በወቅቱ ለማግኘት የታሰበው 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ቢሆንም የህገ ወጥ ንግድ መስፋፋትና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ጥራት የሚጠበቀውን ያህል ባለመሆኑ ማሳካት አልተቻለም ተብሏል። ከተያዘው እቅድ 57 በመቶ ሲሆን ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ85 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ ተመዝግቧል። 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላሩ የተገኘው ኤሌክትሪክ፣ የቅባት እህሎች፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች፣ ቡና፣ ወርቅ የመሳሰሉ የግብርናና የማኑፋክቸሪንግ ምርቶችን ወደ 140 አገሮች በመላክ መሆኑን ገልፀዋል። ወደ ቻይና፣ አሜሪካ፣ ሶማሊያና ሳውዲ አረቢያ የተላኩ ምርቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ። ከተገኘው ገቢ ውስጥም የግብርና ምርቶች 67 በመቶ ድርሻ በመያዝ ቀዳሚ ሲሆን የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች እና ማዕድኖች ሁለተኛ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል ብለዋል። ኤሌክትሪክ፣ የቅባት እህሎች፣ ሻይና ቡና፣ ባህርዛፍና ጫት ከእቅዳቸው 75 በመቶ በላይ ማሳካት የተቻለ ሲሆን አትክልትና ፍራፍሬ፣ የቁም እንስሳት፣ ወርቅና ሌሎች ማዕድናት ከ50 በመቶ በታች በመሆን ዝቅተኛ አፈፃፀም እንዳሳዩ ጠቁመዋል። ለዚህም ምክንያቱ በግብርና ምርቶች ላይ የምርት ጥራት የሚጠበቀውን ያህል አለመሆን፣ የቁም እንስሳትና ወርቅ ላይ ህገ ወጥ ንግድ በመስፋፋት መሆኑን ጠቅሰዋል። በቀሪ ወራት ጉድለቱን ለመሸፈን የግብርና ምርቶች በወቅቱ በተሻለ ጥራትና መጠን ለገበያ እንዲቀርቡ ለማድረግ እንዲሁም እሴት ጨምሮ መላክ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። 'ህገ ወጥ ንግዱን ለመከላከልም መንግስት በየአካባቢው እስከ ቀበሌ ድረስ ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ እየሰራ ነው' ብለዋል። በሌላ በኩል በአገሪቱ ተከስቶ የነበረውን የዱቄትና የዳቦ አቅርቦት ችግር ለመፍታት መንግስት ልዩ ድጎማ አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ለዳቦ ስንዴ የሚወስዱ ፋብሪካዎች ከኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ጋር በማስተሳሰር ህብረተሰቡ ላይ የሚመጣውን ተጨማሪ ክፍያ መንግስት ይሸፍናል ብለዋል። በአገር ውስጥ ተሰብስቦ ከተገዛው ምርት በተጨማሪ ችግሩን ለመቅረፍ ከውጭ አራት ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለመግዛት ሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ በወር 624 ሺህ ኩንታል ሲሰራጭ የነበረው ስንዴውን ለመግዛት የወጣው ጨረታ ሁለት ጊዜ ባለመሳካቱ በሚያዚያ ወር በግማሽ ቀንሷል ብለዋል አሁን ላይ አራት ሚሊዮን ኩንታሉ በአስቸኳይ እንዲገዛ በመንግስት ውሳኔ ማሳለፉን ገልጸዋል። እጥረቱን ለመቀነስ ከብሄራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በጊዜያዊነት እህል በመበደር ለማከፋፈል ጥረት መደረጉን ጠቁመዋል። ከውጭ አገር 555 ሺህ 500 ኩንታል ስንዴ ተገዝቶ ወደ አገር ውስጥ እየገባ መሆኑን የገለጹት አቶ ወንድሙ 'ያለምንም መስተጓጎል ለፋብሪካዎችና ለግለሰቦች ይከፋፈላል' ብለዋል። መንግስት ተገቢውን ድጎማ እያደረገ እንደሆነ ያስታወሱት ኃላፊው 'ስንዴ የለም በሚል ሰበብ የዳቦ መጠን ቀንሰው በሚያመርቱና የዱቄት ዋጋ የሚጨምሩ ካሉ በሚደርሰው ጥቆማ መሰረት ርምጃ ይወሰዳል' ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም