በአዲስ አበባ ለኮሮና ቫይረስ ሕሙማን የሚውል የፊልድ ሆስፒታል ተገነባ

54

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) ለበርካታ የኮሮና ቫይረስ ሕሙማን ሕክምና መስጫ የሚውል 'አዲስ አበባ ኮቪድ-19 ፊልድ ሆስፒታል' ተገነባ።

በቅርቡ ሥራ የሚጀምረውን ሆስፒታል የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰና የዓለም የምግብ መርኃ ግብር ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስሌይ መርቀው ከፍተውታል።

በቦሌ ቡልቡላ አካባቢ የሚገኘው ይህ የፊልድ ሆስፒታል 25 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን በዓለም የምግብ መርኃ ግብር ድጋፍ የተሰራ ነው ተብሏል።

በሦስት ሣምንታት ውስጥ የተገነባው ሆስፒታሉ ቀሪ የማጠናቀቂያ ሥራዎች ተከናውነውለት ከ10 ቀናት በኋላ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ተገልጿል።  

ሆስፒታሉ በተለያየ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የኮሮና ቫይረስ ሕሙማን ሕክምና መስጫነት የሚውል ሲሆን በዓለም ጤና ድርጅት የጥራት ደረጃ መሰረት መገንባቱ ተጠቁሟል።

ዶክተር ሊያ እንደተናገሩትም ሆስፒታሉ በዓለም የምግብ መርሃ ግብር፣ በዓለም ጤና ድርጅት እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቅንጅት የተገነባ ነው።

ለድንገተኛ ሕክምና በአጭር ጊዜ የተገነባ ቢሆንም ለረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት የሚችል ማዕከል መሆኑን ገልጸዋል።  

ሆስፒታሉ ቀደም ሲል ለመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች ተብሎ የተሰራ ቢሆንም ለሌሎች ሕክምና መስጫ ሆኖ እንዲያገለግልም እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከቀናት በኋላ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆንና ሆስፒታሉን ለሌሎች የጤና አገልግሎት ሥራዎች ለማዋል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እየተካሄደ እንደሆነም ዶክተር ሊያ ጠቁመዋል።

የዓለም የምግብ መርኃ ግብር ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስሌይ የኢትዮጵያ መንግሥት ቫይረሱን ለመከላከል ከፍተኛ ትኩረት አድርጓል ሲሉ ተናግረዋል።

በተለይም የኢትዮጵያ መንግሥት ሆስፒታሉን ከተቋማቸውና ከመንግሥታቱ ድርጅት ጋር በመሆን እውን ማድረጉን አድንቀዋል።

በሦስት ሳምንታት ውስጥ ይህን ማብቃት መቻሉ የሚደነቅ ነው በማለት።

ለዚህ ስኬት በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የአሰራር ሥርዓቶችን ማቅለል መቻላቸው መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም