የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ቀደም ሲል የወጣው መመሪያ ተሻሻለ

89

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2012(ኢዜአ) በሀገሪቱ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተላለፉ መመሪያዎችን ለመተግበር የሚታዩ መዘናጋቶችንና ትኩረት ያለመስጠት ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ቀደም ሲል የወጣውን መመሪያ ማሻሻሉ ተገለጸ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስተወቀው በሀገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተበት እለት ጀምሮ በመንግስትና በባለድርሻ አካላት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንና ትዕዛዞች፣ ክልከላዎችና መልዕክቶች እየተላለፉ ነዉ፡፡

ይሁንና በቅርቡ በመንግስት ተቋማት፣ በልማት ድርጅቶችና በግል ተቋማት ወስጥ በተደረገ ምልከታ ቅድመ ጥንቃቄዎችን ከመተግበር የመዘናጋት፣ ትኩረት ያለመስጠት ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ መረጋገጡንም በመግለጫው ተጠቅሷል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ቀደም ሲል የወጡ መመሪያ ቁጥር 1/2012 እና መመሪያ ቁጥር 2/2012 ማሻሻያዎችን የያዘ መመሪያ ቁጥር 4/2012ን አፅድቆ ስራ ላይ እንዲውል አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡

ይን መነሻ በማድረግም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚኒስትሮች ኮሚቴ ቀደም ሲል ያወጣውን መመሪያ ማሻሻሉን በመጥቀስ፤ በመመሪያ ቁጥር 4 በኮድ 2 በቤት ተሸከርካሪዎች ተጥሎ የነበረዉ ከፊል የእንቅስቃሴ ክልከላ፣ የማስክ አጠቃቀም፣ በአገር አቋራጭ የህዝብ ተሸከርካሪዎች ላይ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች መግቢያና መዉጫ ስአት ላይ ማሻሻያ መደረጉ ተገልጿል።


በተሻሻለዉ መመሪያ መሰረት ከቤት ዉጭ በማንኛዉም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ማድረግ ግዴታ እንዲሆን ወስኗል፡፡


የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ በፋብሪካዎች የተሰራ ወይም ባህላዊ ጨርቅ ሊሆን እንደሚቻል የጠቀሰው መግለጫው፤ ይህን ግዴታ ለማስፈጸም የጸጥታ መዋቅሩ ኃላፊነት እንዳለበት ተወስኗል፡፡

በኮድ ሁለት የቤት ተሸከርካሪዎች ተጥሎ የነበረዉ ክልከላ ተነስቶ አጠቃላይ የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን ለመገደብ የሚያስችል አማራጭ ክልከላ እንድተገበር በሚኒስትሮች ኮሚቴ መወሰኑም ተገልጿል።

በሌላ በኩል የትራንስፖርት መጨናነቅን ለመቀነስ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች የስራ መግቢያ ስአት 1፡30 እንዲሆን የተቀመጠ ሲሆን መዉጫ ስአቱም 9፡30 እንዲሆን ተደርጎ ተሸጋሽጓል ብሏል መግለጫው።


ከኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መግለጫ ሙሉ ቃል

---------------------------------
በአገራችን የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተበት እለት ጀምሮ በመንግስትና በባለድርሻ አካላት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን ትዕዛዞች፣ ክልከላዎችና መልዕክቶች እየተላለፉ ነዉ፡፡ እነዚህን መልእክቶችና ትእዛዞች ሰምቶ ለራስ በመፈጸምና ሌሎች እንዲፈፅሙት በማድረግ በኩል በአንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሻሉ ሁኔታዎች ቢኖሩም ነገር ግን በርካታ በሚባለዉ ህብረተሰቡ ዘንድ የመዘናጋት፣ የቸልተኝነትና በሽታዉን አስመልክቶ የሚሰጡ ትእዛዛቶች ወደ ጎን በመተዉ የሚሰጡ መግለጫዎችን የመላመድና ትኩረት ያለመስጠት ሁኔታዎች እየተስተዋለ ይገኛል፡፡

በቅርቡ በመንግስት ተቋማት፣ በልማት ድርጅቶችና በግል ተቋማት ወሰጥ ያደረግነዉ ምልከታ ከቅደመ ጥንቃቄ ጋር በተያያዘ የመዘናጋት፣ ትኩረት ያለመስጠት ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ ለማረጋገጥ ችለናል፡፡

ማህበረሰባችን በተለያዩ ቦታዎች ላይ በተለይም በግብይት ቦታዎችና በትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ አካባቢ እያሳየ ያለዉ መዘናጋትና ህጎቹን ያለማክበር ጉዳይ አሳሳቢ ነዉ፡፡ ይህ የኮሮና ቫይረስ በአገራችን በተገኘበት እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት ሰሞን የነበሩ ጥንቃቄዎች ጋር ስነጻጸር እየቀነሰ መዘናጋት እየጨመረ ሲሆን በተቃራኒዉ አሁንም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ እጅጉን አሳሳቢና ዋጋ የሚያስከፍል ጉዳይ እየሆነ ይገኛል፡፡

መንግስት በሽታዉን ለመከላከልና ስርጭቱን ለመቀነስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አዉጆ ደንብና መመሪያዎችን በማዉጣት ተግባራዊ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ከዚህ ቀደም የወጡ መመሪያ ቁጥር 1/2012 እና መመሪያ ቁጥር 2/2012 ማሻሻያዎችን የያዘ መመሪያ ቁጥር 4/2012ን አፅድቆ ስራ ላይ እንዲዉል አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡


በዚሁ መሰረትም በመመሪያ ቁጥር 4 በኮድ 2 በቤት ተሸከርካሪዎች ተጥሎ የነበረዉ ከፊል የእንቅስቃሴ ክልከላ ፣የማስክ አጠቃቀም ፣ በአገር አቋራጭ የህዝብ ተሸከርካሪዎች ላይ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች መግቢያና መዉጫ ስአት ላይ ማሻሻያ አድርጓል፡፡


የኮድ ሁለት የቤት ተሸከርካሪዎች ላይ መጣል ሚገባው የትራንስፖርት ሚኒስቴር በኩል የተደረገውን ጥናት መነሻ በማድረግ በከፊል በመገደብ ግለሰቦች ቤታቸዉ እንዲዉሉ በማድረግ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ታሳቢ ተደርጎ በሙሉና በጎዶሎ መለያ ቁጥር ከፊል እገዳ ተጥሎ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን ሆኖም የኮድ 2 ተሸከርካሪ ባለቤቶች በታሰበዉ መልኩ ቤታቸዉ ከመዋል ይልቅ የህዝብ ትራንስፖርት በመጠቀም እና ታርጋዎችን እየቀያየሩ የመጠቀም ሁኔታ መታየቱ እንዲሁም ተራቸዉ ባልሆነ ቀን ቤታቸዉ ከመዋል ይልቅ በሰፊዉ የመንቀሳቀስ ሁኔታ የተስተዋለ መሆኑ ክልከላዉን መልክ መቀየር አሰፈላጊ ሆኗል፡፡


በመሆኑም በአጠቃላይ በኮድ ሁለት የቤት ተሸከርካሪዎች ተጥሎ የነበረዉ ክልከላ ተነስቶ አጠቃላይ የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን ለመገደብ የሚያስችል አማራጭ ክልከላ እንድተገበር የሚኒስትሮች ኮሚቴ ወስኗል፡፡

የእንቅስቃሴ ገደብ መቀነሻ አሰራሮች አንዱ የሆነዉ በሀገር አቋራጭ ተሸከሪካሪዎች የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ ነው፡፡ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ሰዎች ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ ለመገደብ አስተዋጽኦ እንደሚያደረግ በትራንስፖርት ሚኒስቴር የተደረገው ጥናት ያመላክታል፡፡

በዚሁ መሰረት አገር አቋራጭ የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች መደበኛ የወንበር አቅማቸዉ ከ45(አርባ አምስት) ሰዉ በላይ የሆነ ተሸከርካሪዎች የሚያስከፍሉት የታሪፍ ጭማሪ ከመደበኛ ዋጋዉ 75% እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን መደበኛ የወንበር ቁጥራቸዉ እስከ (45) አርባ አምስት ሰዉ የሆኑ የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች የሚያስከፍሉት የታሪፍ ጭማሪ ደግሞ 100% መሆኑ ተወስኗል፡፡

በተያያዘ የሚኒስትሮች ኮሚቴ በተሻሻለዉ መመሪያ መሰረት የማስክ አጠቃቀምን አስመልክቶ ከቤት ዉጭ በማንኛዉም ቦታ የአፍና አፈንጫ መሸፈኛ ማስክ ማድረግን ግዴታ እንዲሆን ወስኗል፡፡

የአፍና አፈንጫ መሸፈኛ ማሰክ በፋብሪካዎች የተሰራ ወይም ባህላዊ ጨርቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን ግዴታ በማስፈጸም ረገድ የጸጥታ መዋቅሩ ኃላፊነት እንዳለበት ተወስኗል፡፡

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች የስራ መግቢያ ስአት 1፡30 እንዲሆን የተቀመጠ ሲሆን መዉጫ ስአቱም 9፡30 እንዲሆን ተደርጎ ተሸጋሽጓል፡፡ ይህም የትራንስፖርት መጨናነቅ ለመቀነስ ነው፡፡

በአጠቃላይ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሁሉም ህብረተሰብ ኃላፊነትና ግዴታ ያለበት በመሆኑ የሚታዩ መዘናጋቶችን እና ችላ ባይነትን በመቅረፍ ሁላችንም ህግና ሥርዓቱን ማክበር ግዴታ እንደሆነ በመገንዘብ መላዉ የሀገራችን ህዝብ እራሱ፣ቤተሰቡንና ሀገሩን የኮሮና ቫይረስ ከሚያስከትለው ጉዳት ለአፍታም ሳይዘናጋ ለመጠበቅ ርብርብ እንዲያደረግ ጥሪያችንን እናቀረባለን፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ
ቀን፡- ግንቦት 19 ቀን 2012 ዓ.ምአዲስ አበባ ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም