ናሽናል አቪየሽን ኮሌጅ በበይነ መረብ አማካኝነት እያስተማረ ነው

96

 አዲስ አበባ ግንቦት 19/2012 (ኢዜአ) በኮሮናቫይረስ  ወረርሽኝ ምክንያት የገጽ-ለገጽ ትምህርት ያቋረጠው ናሽናል አቪየሽን ኮሌጅ በበይነ መረብ  እያስተማረ መሆኑን ገለጸ።

ኮሌጁ ለ90 አነስተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦች የምግብና ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚውል ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡

ኮሌጁ በኦንላይን ለማስተማር የሚያስችል ደረጃውን የጠበቀ የሶፍት-ዌር ፈቃድ በመግዛት ወደ ስራ ማስገባቱን ገልጿል፡፡

ተማሪዎች ከመምህራኖቻቸው ጋር በቀጥታ በበይነ መረብ አማካኝነት ግንኙነት በማድረግ ያላቸውን ማንኛውን ጥያቄ ማቅረብ እንዲችሉና ምላሽ እንዲያገኙ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን ተነግሯል፡፡

የናሽናል አቪየሽን ኮሌጅ እና የናሽናል አየር መንገድ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ብሩ እንደገለጹት፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ስርጭት ለመቀነስ የገጽ ለገጽ ትምህርት እንዲቋረጥ የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ኮሌጁ ተማሪዎች በኦንላይን ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አድርጓል።

በዚህም ኮሌጁ የሚሰጠው ትምህርት ሳይቋረጥ መቀጠሉን አመልክተዋል።

የተዘረጋው አሰራርም የመማር ማስተማር ሂደቱን ከማስቀጠሉ በተጨማሪ የሰራተኞችን የስራ ዋስትና እና ጤንነት ለመጠበቅ እንዳስቻለ ገልጸዋል፡፡

ኮሌጁ ከመማር ማስተማር ስራው በተጨማሪ ማህበራዊ ኃላፊነት የመወጣት ግዴታ እንዳለበት ያመለከቱት ምክትል ስራ አስኪያጁ፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ችግር ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ተሳትፎ እያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህም በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ውስጥ ለሚገኙ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦች የምግብና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ እርስ በርስ በመደጋገፍ ይህንን ወቅት ማሳለፍ እንዳለበት የገለጹት አቶ ገዛኸኝ፤ ህብረተሰቡ ራሱንና ወገኑን ከወረርሽኙ ተጋላጭነት ለመጠበቅ የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክት በአግባቡ እንዲተገብር መክረዋል።

የየካ ክፍለ ከተማ ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ብስራት መጀሬ በበኩላቸው ''የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ሁሉም ወገን መተባበርና ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል'' ብለዋል።

ህብረተሰቡም በአግባቡ የእጅ ንጽህናውን መጠበቅ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ መጠቀምና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና ተቋማትም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመደገፍ የሚያደርጉት ጥረት ምስጋና እንደሚገባው ገልጸው፤ ናሽናል አቪየሽን ኮሌጅ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

ድጋፉ የተደረገላቸው ቤተሰቦችም ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በድጋፍ ርክክቡ ወቅት 45 የኮሌጁ ተማሪዎችና የኮሌጁ ሰራተኞች ደም ለግሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም