ሚኒስቴሩ ከ219 ሺህ በላይ ዜጎችን ከጎዳና ለማንሳት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ

64

 አዲስ አበባ ግንቦት 19/2012 (ኢዜአ) የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴርና ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ከ219 ሺህ በላይ ዜጎችን ከጎዳና ለማንሳት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።

የመግባቢያ ሰነዱ 219 ሺህ 450 ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶችን ከጎዳና ላይ ለማንሳት የሚያስችል መርሃ ግብር ለመጀመር የተፈረመ ነው።

ቀደም ሲልም ከኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ጋር በመሆን በጎዳና ላይ የነበሩ ዜጎችን የማንሳት ሥራ መሠራቱን ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ ገልጸዋል።

ለእነዚህ ዜጎች የምክር አገልግሎትና የክህሎት ስልጠና በመስጠት በገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ በማሰማራት ህይወታቸው እንዲለወጥ መደረጉንም ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ ዛሬ ከአሶሴሽኑ ጋር የተፈራረመው የመግባቢያ ሰነድም 219 ሺህ 450 ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶችን በአራት ዓመታት ውስጥ ከጎዳና ማንሳት እንደሚያስችል ነው የገለጸው።

የኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተር ወይዘሮ ቅድስት በቀለ በበኩላቸው፤ ተቋሙ ከ122 ሺህ በላይ ዜጎችን ከጎዳናና ከልመና ህይወት እንዲላቀቁ ማድረጉን ገልጸዋል።

በመግባቢያ ሰነዱ መሰረት በመጀመሪያው ዙር 20 ሺህ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ከጎዳና ተነስተው ወደ ማዕከሉ እንደሚገቡ አስረድተዋል።

ከጎዳና የሚነሱት ዜጎች በመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት  የስነ-ልቦና ስልጠና እንደሚያገኙና በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ደግሞ የክህሎት ስልጠና እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።

በዚህም ገቢ በሚያስገኙ ሥራዎች ተሰማርተው ራሳቸውን በኢኮኖሚ እንዲደግፉና ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ለማስቻል እንደሚሠራ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም