የመስኖ ልማት ባህል አለመዳበር አርሶ አደሩ የእለት ጉርሱ እንኳን እንዳያሟላ አድርጓል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

68
አዲስ አበባ ሰኔ 29/2010 የመስኖ ልማት ባህል አለመዳበር አርሶ አደሩ ከእለት ጉርሱ አንስቶ ፍላጎቱን እንዳያሟላ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ እየሰጡ ነው። አርሶ አደሩ መስኖን ተጠቅሞ ለራሱና ለዓለም ገበያዎች ማቅረብ የሚያስችል ስትራቴጂ ተቀርጾ እየተሰራ ቢሆንም የመስኖ ልማት አጠቃቀማችን ዝቅተኛ በመሆኑ የታሰበውን ያህል ጥቅም አለመገኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። መስኖ የማልማት ባህል አለመዳበሩ አርሶ አደሩ የእለት ጉርሱን በሚፈለገው ደረጃ እንዳያደርስ አድርጓልም ብለዋል። በበጀት ዓመቱ መንግስት የግብርናውን ዘርፍ ለማሳለጥ የሰጠው ትኩረት የላቀ ቢሆንም ውጤታማነቱ በቂ አይደለም። በዚህም ውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር በዘርፉ አገሪቱ ልትደርስ የሚገባትን ያክል ርቀት  ማድረስ ላይ በትኩረት መስራት እንዳለበት ገልጸዋል። ከአዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለዘርፉ የሚገኘውን ድጋፍ ለታለመለት አላማ ከማዋል አኳያም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተከታትሎ ከማስፈጸም አንጻር ያለበትን ክፍተት በመፍታት ዘርፉን ማበልጸግ ይገባልም ብለዋል። በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘርፉ ማደግ የሚገባውን ያህል አለማደጉ ብቻ ሳይሆን በሁለተኛው እቅድ ዘመን አጋማሽ ላይም ለውጥ አለመምጣቱ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያል። ለምክር ቤቱ አባላትም ወደ አካባቢዎቻቸው ሲመለሱ አርሶ አደሩ የሚያስፈልጓቸውን መሰረታዊ ፍላጎቶችንና ሊደረግላቸው የሚገባውን ድጋፎች በመለየት ዘርፉን እንዲያግዙ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም