የጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን ድንበር አቋርጠው የሚገቡ ሰዎች ጉዳይ አሳስቦታል

115

 አዲስ አበባ ግንቦት 19/2012 (ኢዜአ) በርካቶች በኮቪድ-19 ከሚያዙባት ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው ወደ ክልሉ የሚገቡ ዜጎች ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ከ800 በላይ ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸውንና 8 ሰዎችም መሞታቸውን ዛሬ የወጣ መረጃ ያሳያል።

እስካሁን በቫይረሱ የተያዘ ሰው ያልተመዘገበበት የጋምቤላ ክልል ከዚህች ጎረቤት አገር ጋር በሰፊ ድንበር ይዋሰናል።

ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በተገበረችው የአስቿኳይ ጊዜ አዋጅ በድንበር አካባቢ የሰዎች እንቅስቃሴ ተገድቧል።

ይሁን እንጂ የድንበሩን ስፋት ተገን በማድረግ በየዕለቱ በርካታ ቁጥር ያላቸው ደቡብ ሱዳናዊያን ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ለኢዜአ ገልጿል።

ኮሚሽነር ኢፒያንግ ኦቻን እንደሚሉት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በድንበር በኩል የሰዎች እንቅስቃሴ ይገደብ ቢባልም ከደቡብ ሱዳን ጋር ሰፊ ድንበር ላለው የጋምቤላ ክልል ሁኔታው ከባድ ሆኗል።

ዋናዋና የተባሉ መግቢያ በሮችን መዝጋት ቢቻልም ሰዎች በተለያዩ ቦታዎች ሾልከው እየገቡ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

በደቡብ ሱዳን የተከሰተውን የእርስ በእርስ ግጭት ሽፋን በማድረግ 'ስደተኛ ነኝ' በማለት ድንበር የሚያቋርጡ ሰዎችም በዝተዋል ነው የሚሉት።


በድንበሩ አካባቢ የሚኖሩ የሁለቱ አገራት ብሔረሰቦች ተመሳሳይ መሆንም አንዱን ከሌላው ለመለየት አዳጋች እንዳደረገው ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

ከክልሉ በተጨማሪ የፌዴራል የፀጥታ አካላት በድንበር አካባቢ መኖራቸውን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ ያም ሆኖ የታሰበውን ያህል ውጤት አልተገኘም ይላሉ።

የፌዴራል መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት ተረድቶ በአገራቱ የድንበር አካባቢ በጊዜያዊነትም ቢሆን የ'ይለፍ ወረቀት' መስጠት ቢጀመር የተሻለ ይሆናል ሲሉም ጠቁመዋል።


ከኢትዮጵያ ከሚዋሰኑ የምስራቅ አፍሪካ አገራት አብዛኞቹ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠቁ ይገኛሉ።

ከእነዚህ መካከልም እስከ ዛሬ ባለው ሪፖርት ሱዳን 4 ሺህ 146 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙባት ሲሆን 184ቱ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በጅቡቲም 2 ሺህ 468 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፣ 14ቱ ህይወታቸውን አጥተዋል፤ በኬንያ 1 ሺህ 348 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው 58 ሰዎች በዚሁ ሳቢያ ለሕልፈት ተዳርገዋል።

በሶማሊያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 711 ሲሆን 67ቱ ህይወታቸውን አጥተዋል፤ በኤርትራ በተለየ ሁኔታ 39 ሰዎች ብቻ ናቸው በቫይረሱ የተያዙት።

ኢትዮጵያ ከእነዚህ አገራት ጋር በሰፊ የመሬት ድንበር የምትዋሰን በመሆኗ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ አላመለጠችም፤ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም