ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የኮቪድ-19 መከላከያ ግዥ ሲፈጽሙ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

52

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ኮቪድ-19ን ለመከላከል የምትፈጽሟቸው ግዥዎች ለኦዲት ግኝት ተጠያቂነት እንዳያጋልጧችሁ ጥንቃቄ አድርጉ ሲል የፌዴራል ዋና ኦዲተር አሳሰበ።

የተቋማት ኃላፊዎች ግዥዎች በእነርሱ እውቅና ስለመፈጸማቸው ማረጋገጥ አለባቸውም ብሏል።

ወትሮም የኢትዮጵያ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በዓመቱ መጨረሻ ለከፍተኛ የኦዲት ግኝት እንደሚጋለጡ የዋና ኦዲተር መረጃ ያመላክታል።

የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል እየተፈጸሙ ያሉ ግዥዎች ለሙስና ሊጋለጡ እንደሚችሉ ባካሄደው አስቸኳይ የዳሰሳ ጥናት ማረጋገጡን ገልጿል።

በተመሳሳይ የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር 'የታቀደ ግዢ እንኳን ሲፈጽሙ ለኦዲት ግኝት የሚጋለጡት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የአሁኑ መደበኛ ያልሆነ ግዥ ለሙስና ያጋልጣቸዋል' የሚል ስጋት አድሮበታል።

ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ ለኢዜአ ሲናገሩ "ነገሩ ተባብሶ ተቋማት ተጠያቂ ከመሆናቸው በፊት ከወዲሁ ጥንቃቄ ይደረግ" ሲሉ አሳስበዋል።

"በዚህ ጊዜ የተቋማት ኃላፊዎች ከሁሉ በላይ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው" ያሉት ዋና ኦዲተሩ በጣም አስፈላጊ ካልሆነ በቀር ግዥ ባይፈጸም ይመረጣል ነው ያሉት።

ጥንቃቄው እንደ መንግስትም እንደ አገርም ያለውን የሃብት እጥረት በአግባቡ መጠቀሙ ቀጥሎ የሚመጣውን ከባድ ጊዜ ለማለፍ እንደሚረዳ በመጠቆም።

የመንግስት ተቋማት ኃላፊዎች ይህን ሁኔታ ከወትሮው በተለየ መልኩ ሊያዩትና ሊከታተሉት እንደሚገባም መክረዋል።

አቶ ገመቹ በተጨማሪም በግዥ ሂደት ዋና ተሳታፊ የሆነው የገንዘብ ሚኒስቴር ለመስሪያ ቤቶች በሚለቀቀው ገንዘብ ላይ የተለየ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚኖርበት ጠቁመዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ሚኒስቴሩ አሳማኝ ካልሆነ በቀር ገንዘብ መልቀቅ የለበትም፤ ተቋማትም በማዕቀፍ ከተለዩ አቅራቢዎች ብቻ ግዥ መፈጸም አለባቸው። 

ግዥ ብቻ ሳይሆን ወረርሽኙን ለመከላከል በእርዳታ መልክ የሚደረጉ ድጋፎችም በተማከለ አሰራር ለሚፈለገው ዓላማ ሊውሉ ይገባል ባይ ናቸው።

ሁሉም ነገር በተማከለ መልኩ ወደ አንድ ቋት እየገባና ከዚያ እየወጣ የሚሰራጭበት ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባም ዋና ኦዲተሩ ምክረ ሃሳብ ሰንዝረዋል።

ይህ ሳይሆን ቀርቶ የኦዲት ችግር ካጋጠመ ግን በቅድሚያ ተጠያቂ የሚሆኑት የተቋማት ኃላፊዎች እንደሚሆኑም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም