የአስቸካይ ጊዜ አዋጁ ሳይሸራረፍ ተግባራዊ እናደርጋለን ....የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች

99

አርባ ምንጭ ግንቦት 19/2012 (ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለጤንነታችንና ለደህንነታችን ያለው አስፈላጊነት ወሳኝ በመሆኑ ሳይሸራረፍ ተፈፃሚ እናደርጋለን ሲሉ አስተያዩተያቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። 

በአርባ ምንጭ ከተማ የውሃ ምንጭ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ታሪኩ እስራኤል በሰጡት አስተያየት  አዋጁ  ህዝቡን ከወረርሽኝ ለመታደግ ታስቦ የወጣ የደህንነታችን ዋስትና ነው።

ስለሆነም ለተፈፃሚነቱ  ካለምንም ቅድመ  ሁኔታና  የውዴታ ግዴታ  በእለት ተእለት ኑሮአችን አክብረን ልንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል።

ያለበለዚያ ወረርሽኙ በንክኪ የሚተላለፍ እንደመሆኑ መጠን ጥንቃቄ ካላደረግን ለአደጋ የምንጋለጠው እኛና ቤተሰቦቻችን ናቸው ያሉት አቶ    ታሪኩ  አካላዊ ርቀታችን ጠብቀን እንድንቀሳቀስ መደረጉ ተገቢ ነው።

የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት በተለይ በአርባ ምንጭ ከተማ ሲቀላ ገበያ ላይ የነበረው የአትክልትና ፍራፍሬ ገበያ ወደ ሌላ ስፍራ ማዛወሩ ከስጋት  እንዳላቀቃቸውም ተናግረዋል።

የቫይረሱ ስርጭት በአገራችን እየጨመረ ከመምጣቱ አንፃር የህብረተሰቡ ግዴለሽነት ግን ስጋት እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።


ዜጎችን ከወረርሽኝ ለመታደግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ተገቢ ቢሆንም አፈጻጸሙ ግን ደካማ ነው ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ፀሐይ ጎበና የተባሉ የዕድገት በር ቀበሌ ነዋሪ  ናቸው።

እሳቸው እንደሚሉት ቫይረሱ በአገራችን በተከሰተ በጥቂት ጊዜ ውስጥ  በንጽህናውም ሆነ ለአካላዊ ርቀቱ ትኩረት የተሰጠው ቢሆንም ጥንቃቄ የሚያደርጉት ግን ጥቂቶች መሆናቸውን ታዝበዋል።

የአንዱ አለመጠንቀቅ ግለሰቡን ብቻ ሳይሆን ሌላውንም ጭምር የሚጎዳ በመሆኑ ለህዝብ ደህንነት ሲባል የወጣን አዋጅ ካለምንም መዘናጋት  ልናከበረው ይገባል ብለዋል ።

በግላቸው ሰውን እንደማይጨብጡ፣ አካላዊ ርቀትን እንደሚጠብቁና ግደታ ካልሆነ በቀር ከቤት እንደማይወጡም ነው ያመለከቱት።

በአርባ ምንጭ ከተማ የጤና ባለሙያ የሆኑት አቶ ፍሬው ደለለኝ በበኩላቸው ለሰው ልጆች ከጤና በላይ የተሰጠ ትልቅ ፀጋ የለም ይላሉ።

በመሆኑም ነገ መልሰን ለምናገኘው ማህበራዊ ህይወት ከመጨነቅ ይልቅ ቅድሚያ ለጤንነታችን መጠበቅ ትኩረት በመስጠት የአዋጁን ክልከላዎች አክብረን ልንቀሳቀስ ይገባል የሚል መልእክት አስተላልፈዋል ።

የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ዳንኤል አረጋ አዋጁ ሰፊውን ህዝብ ከቫይረሱ ለመታደግ እንጂ መብት ለማሳጣት ተብሎ የወጣ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

በአዋጁ ምክንያት ከምናጣው መብት ይልቅ የምናገኘው ጥቅም የሚበልጥ በመሆኑ ፖሊስ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጎን ለጎን  ህግን ለማስከበር እንደሚተጋ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም