በጎንደርና መተማ ለኮሮና መከላከል ድጋፈ ተደረገ

57

ጎንደር/ መተማ (ኢዜአ )ግንቦት 19 /2012. በመተማና አካባቢው በተቋቋሙ የለይቶ ማቆያዎች የሚስተዋለውን የግብዓት እጥረት ለማገዝ 660 ሺህ ብር ግምት ያላቸው የምግብ እህልና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉ ተገለፀ።

በአሜሪካ የሚኖሩ የጎንደርና አካባቢው ተወላጆች በመተማ አካባቢ በኮሮና በሽታ ምክንያት በለይቶ ማቆያ ማእከል ለሚገኙ ወገኖች የሚውል ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ እህል ድጋፍ ትናንት አድርገዋል፡፡

ድጋፉም በለይቶ ማቆያው ለሚገኙ ወገኖች የምግብ ፍጆታ የሚውል 227 ኩንታል የፍርኖ ዱቄት ነው።

ለማዕከሉ የተላከውን ድጋፍ የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ የተረከቡ ሲሆን ይህም እንደ ሀገር የገጠመንን የጤና ችግር ለመቆጣጠር ያግዛል።

የበሽታው ተጋላጭ የሆነው የህብረተሰብ ክፍል ለመታደግ በሃብት አሰባሰብ በኩል ቢሮው ከአጋር አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ነው።  

የምእራብ ጎንደር ዞን ከሱዳን ጋር ባለው ሰፊ የድንበር ወሰን የሚገቡና የሚወጡ ሰዎችን ለመቆጣጠር ክልሉ የተጠናከረ ክትትል እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በዞኑ በተቋቋሙ 6 የለይቶ ማቆያ ማእከላት ሱዳን ሀገር ቆይተው የተመለሱ ከ600 በላይ ሰዎች እንደሚገኙም የቢሮ ሃላፊው አስታውቀዋል፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር 160 ሺህ ብር ግምት ያለው ቁሳቁስ ለዞኑ ድጋፍ ማድረጉን የገለፁት ደግሞ በማህበሩ የሰሜን ጎንደር ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ አታለል ታረቀኝ ናቸው።

ማህበሩ ለሶስተኛ ጊዜ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው በዛሬ እለትም በመተማ ለይቶ ማቆያ ማእከላት ያለውን የቁሳቁስ እጥረት ለማሟላት 100 ፍራሽ፣ ሁለት ሺህ ሳሙና፣ የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር፣ ምንጣፍና ብርድ ልብስ ያካተተ ድጋፍ ተደርጓል።

ማህበሩ የቁሰቁስ ድጋፉን ያደረገው ከዴን ማርክ የቀይ መስቀል ማህበር ጋር በመተባበር መሆኑን የጠቀሱት ስራ አስኪያጁ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሁሉም ባለድርሻ አካላትና ድርጅቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል ።

የዞኑ ኮሮና መከላከል ግብረ ሃይል አባል አቶ ብርሃኑ መንገሻ በበኩላቸው በዞኑ በሚገኙ ስድሰት የለይቶ ማቆያ ማእከላት የግብዓት አቅርቦት እጥረት አለ።

ይህ ችግር እንዲፈታ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው  የተደረገላቸው ድጋፍ ችግሩን በጊዜያዊነት የሚያቃልል ነው ብለዋል።

ከጤና ሚኒስቴር በተገኘው መረጃ መሰረት በአማራ ክልል እስካሁን በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መካከል 29 የሚሆኑት በመተማ ለይቶ ማቆያ የነበሩ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም