በድንበር አካባቢ ለኮቪድ-19 መከላከል የፌዴራል መንግስት ድጋፍ ወሳኝ ነው

125

ባሀርዳር፤ ግንቦት 18/2012 ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ላይ የስደት ተመላሾች ቁጥር መጨመር የኮሮና ቫይረስ መከላከል ስራውን ከአቅም በላይ ስላደረገው የፌዴራል መንግስትን እገዛ እንደሚፈልግ የአማራ ክልል የኮሮና መከላከል ግብረ-ሃይል አስታወቀ።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብረ-ሃይሉ ስብሳቢ ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ ዛሬ ምሽት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከቱት ኢትዮጵያ በምዕራብ ጎንደር ዞን በኩል ከሱዳን ጋር በምትዋሰንበት ሰፊ ድንበር በርካታ ዜጎች ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ። 

በአዋሳኝ ድንበሩ በሚገኙ 19 የመግቢያ በሮች በእያንዳንዳቸው በቀን እስከ 400 ዜጎች ወደ ክልሉ የሚገቡ በመሆኑ ወደ ለይቶ ማቆያ በማስገባት ጤንነታቸው ተረጋግጦ ወደ ቤተሰቦቸቸው እንዲሄዱ እየተደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል። 

“ከታወቁት የመግቢያ በሮች ውጭም በህገ-ወጥ መንገድ የሚገቡ ሰዎች በርካቶች በመሆናቸው በአካባቢው ለሚገኘው የኮሮና መከላከል ግብረ ሃይል የመከላከል ስራውን አስቸጋሪ አድርጎታል”ብለዋል። 

ከስደት ተመላሾቹ ጋርም የውጭ ሀገራት ዜጎች እንደሚገኙባቸው ገልጸው፤ ችግሩን ለመቋቋም ዩኒቨርሲቲዎች፣ ባለሃብቱና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ካደረጉት ድጋፍ በተጨማሪ የክልሉ መንግስት 150 ሚሊየን ብር በመመደብ የመከላከል ስራውን እያከናወነ እንዳለ አውስተዋል።  

“በዚህም በምዕራብ ጎንደር ስድስት የለይቶ ማቆያ በማቋቋም፣ የቁሳቁስና የሃብት ድጋፍ እያደረገ ቢቆይም አሁን ላይ ከስደት ተመላሹ ቁጥር መብዛት በክልሉ አቅም መሸፈን ከማይቻልበት ደረጃ ደርሷል” ብለዋል። 

“በአካባቢው ካለው የችግሩ ስፋት አንጻር ተጨማሪ በድንበር አካባቢ የአስቸኳይ ጊዜ የለይቶ ማቆያ ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ ከመገኘቱም በላይ የምርመራና የህክምና መስጫ ማዕከላት እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል”ብለዋል። 

ለዚህም ቫይረሱ የተከሰተው ችግር የአንድ አካባቢ ብቻ ሳይሆን የሀገር መሆኑን በመገንዘብ የፌደራል መንግስት፣ ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ የረድኤት ድርጅቶች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል ። 

የአማራ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ የስደት ተመላሾች ጉዳይ ከምዕራብ ጎንደር በተጨማሪ በምስራቅ አማራም ትኩረት የሚሻ መሆኑን መገንዘብ ተችሏል ብለዋል። 

የመተማ ከተማ ከጎንደር 190 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው በመሆኑ በለይቶ ማቆያ የሚገቡ ከስደት ተመላሾች ምርመራ ለማካሄድ ናሙናውን ወደ ጎንደር በማጓጓዝ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን አረጋግጠዋል። 

"ይህም በሰው ሃይል፣ በገንዘብ፣ በጊዜና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ከማሳደሩም በላይ የመከላከል ስራውን አስቸጋሪ በማድረጉ ነው የፌደራል መንግስትን ድጋፍ መጠየቅ ያስፈለገው" ብለዋል። 

በሚደረገው ድጋፍም ተጨማሪ የማቆያ፣ የመመርመሪያና የህክምና ማዕከላት ከማቋቋም በተጨማሪ  በመተማ ከተማ ራሱን የቻለ የአደጋ ምላሽ መስጫ ማዕከል ለማቋቋም መታቀዱን ተናግረዋል። 

የክልሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ገረመው ገብረ ጻድቅ እንዳሉት ኮሮናን ለመከላከል በፌደራል ደረጃ አዋጅ፣ ደንብና ሶስት መመሪያዎች መውጣታቸውን አውስተዋል። 

አዋጁ ላይ በመመስረትም የማስተማርና የህግ ማስከበር ስራ በየደረጃው በሚገኙ የጸጥታና የህግ አካላት እየተሰራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል። 

“አሁን ለይ የበሽታው ስርጭት እየተስፋፋ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በትራንስፖርት፣ በህገ-ወጥ ነጋዴዎችና የተከለከሉ ህጎችን በሚጥሱ አካላት ላይ የተጠናከረ የህግ ማስከበር ስራ ከሚሰራበት ወቅት ላይ ደርሰናል” ብለዋል። 

ለዚህም የህግ ማስከበር ስራውን በአግባቡ ለመምራት ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ አደረጃጀት መዘርጋት መቻሉን ጠቁመው፤ ህብረተሰቡም እያወቀም ይሆን ባለማወቅ ህግን ከመጣስ እንዲቆጠብ አሳስበዋል።              

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም