በአርሲ ዞን የሜካናይዜሽን እርሻ አገልግሎት ተጀመረ

88

አዳማ ፣ ግንቦት 18/2012 (ኢዜአ) በአርሲ ዞን የሜካናይዜሽን እርሻ አገልግሎት ዛሬ በይፋ ተጀመረ፡፡

የእርሻ ሜካናይዜሽን አገልግሎት በተጀመረበት ሥነሥርዓት የፌዴራል መንግሥትና የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ተገኝተዋል።

በዚህ ወቅት የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ  ደበሌ እንደተናገሩት በክልሉ አርሶ አደሩን በኩታ ገጠም በማሰባሰብ ስንዴ፣ የቢራ ገብስና በቆሎ በሜካናይዜሽን የእርሻ መሣሪያዎችና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ ነው።


በአርሲ ዞን በተደራጀ መልኩ ዛሬ የተጀመረው የሜካናይዜሽን እርሻ አገልግሎት ከ300 ሺሀ ሄክታር በላይ መሬት እንደሚሸፍን ገልጸዋል።

ከስምንት ሺህ እስከ 10 ሺህ የኩታ ገጠም አደረጃጀቶችን በስንዴና የቢራ ገብስ ተደራሽ የሚያደርግ አገልግሎት እንደሆነም ጠቅሰዋል።


በተጨማሪም በባሌ፣ ምዕራብ አርሲ፣ ምሥራቅ፣ ሰሜን፣ ምዕራብና ደቡበ ምዕራብ ሸዋ እንዲሁም በአራቱ የወለጋ ዞኖች ላይ ጤፍ፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላና ሌሎችንም ሰብሎች በኩታ ገጠም ለመዝራት እየተረባረብን ነው ብለዋል፡፡


በዘንድሮ የመኸር ወቅት በዘር ከሚሸፈነው ከስድስት ሚሊዮን ሔክታር ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው በሜካናይዜሽንና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን እንደሚሰራም አቶ ዳባ ገልጸዋል።

የሜካናይዜሽን የእርሻ አገልግሎት በይፋ ያስጀመሩት የብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም በበኩላቸው በአርሲ ዞን የተጀመረው አገልግሎቱ ለግብርና ዘርፍ ዕድገት አንዱ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።


"በአርሲ ዞን ለሜካናይዜሽን እርሻ አመቺ መሬት ይዘን ስንዴ ከውጪ ማስገባት አግባብነት የለውም፤ አገልግሎቱን በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሀገር ደረጃ በማስፋት ከውጭ የሚገባውን የግብርና ምርት መተካት አለብን" ብለዋል፡፡


አርሶ አደሩ ከሜካናይዜሽን አገልግሎት ባለፈ በግብዓት አቅርቦት ላይ በተለይ በማዳበሪያና ምርጥ ዘር ያለበትን ችግር ለማቃለል የፌዴራል መንግሥት ተገቢውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

በአርሲ ዞን በኩታ ገጠም ተደራጅተው ለገበያና ለምርጥ ዘር የሚሆን ስንዴ ከአምና ጀምሮ እያመረቱ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አርሶ አደር ፈይሳ ቡታ ናቸው፡፡


አርሶ አደሩ በአርሲ ዞን የጦሳ ወረዳ ባዶሳ ቀበሌ ከ200 ሄክታር በላይ መሬት ከአቻዎቻቸው ጋር በኩታ ገጠም የስንዴ ምርጥ ዘር እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


82 አርሶ አደሮች ሆነው በኩታ ገጠም በመደራጀት የሜካናይዜሽን እርሻ መሣሪያ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን  አስረድተዋል።

በራሳቸው አቅምና በተመቻቸላቸው ብድር ትራክተር በመግዛት ለቀበሌያቸውና ለወረዳው አርሶ አደሮች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


"የቀረበልን ትራክተር በቂ አይደለም" ያሉት አርሶ አደር ፈይሣ ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት መንግሥት ትራክተሮች፣ ማዳበሪያና ፀረ ተባይ መከላከያ በወቅቱ እንዲያቀርብላቸው መፈለጋቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም