የትግራይ ባዮ ቴክኖሎጂ ማዕከል በቲሹ ካልቸር የሥራሥር ፣ ሸንኮራ አገዳና የፍራፍሬ ችግኞችን አፍልቶ እያከፋፈለ ነው

84

መቀሌ፣ ግንቦት 18/2012 (ኢዜአ) የትግራይ ባዮ-ቴክኖሎጂ ማዕከል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ የተለያዩ የሥራሥር፣ ሸንከራ አገዳና ፍራፍሬ ችግኞችን በቲሹ ካልቸር ዘዴ እያፈላ ለተጠቃሚዎች እያቀረበ መሆኑን ገለጸ።

ማእከሉ እያበዛቸው ያሉት የተለያዩ የስራስር ፣ የሸንኮራ አገዳና የፍራፍሬ ዝሪያዎች ከሁሉም የአካባቢ ስነ ምህዳር ጋር የሚስማሙ እና በሽታዎችን የመቋቋም አቅም ያላቸው ናቸው።

ማዕከሉ በቲሹ ካልቸር የቴክኖሎጂ ዘዴ በማፍላትና በማባዛት ለአርሶ አደሮች፣ ለግል ባለሀብቶችና ለተለያዩ ተቋማት በልዩ ትዕዛዝና በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረባቸው ያሉት ዝርያዎች  በምርታማነታቸው የላቁ መሆናቸውን የማዕከሉ ዋና ሥራስኪያጅ  ኢንጂኒየር ሃፍታይ አባዲ ገልጸዋል።

በላብራቶሪ ምርምር ጥራታቸውን የጠበቁና ከበሽታ ነፃ የሆኑ የተለያዩ የዕፅዋት ዝርያዎችን በቲሹ ካልቸር ላብራቶሪ የማባዛት ዘዴ ለባለሀብቶች ጭምር በማቅረብ ላይ መሆኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

''ማዕከሉ በዓመት 40 ሚሊዮን ችግኞችን የማፍላት አቅም አለው''  ያሉት  ኢንጂኒየር  ሃፍታይ ኢትዮጰያ ውስጥ ላሉ የስኳር ፋብሪካዎች  ከፍተኛ ምርት  መስጠት  የሚችሉ  18 ዓይነት የሸንኮራ አገዳ ዝርያዎችን በማባዛት ማቅረቡን ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት ማዕከሉ 85 ሚሊዮን የሸንኮራ አገዳ ችግኞችን በማፍላት ለስኳር  ፋብሪካዎች ማቅረቡን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ለተለያዩ የአገራችን ሥነ ምህዳር  ተስማሚ የሆኑ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን  የሙዝ ችግኞችን በማፍላትና በማባዛት ማሰራጨቱንም አስታውቀዋል።

በትግራይ ባዮ ቴክኖሎጂ ማዕከል የምርምርና ጥራት  ቁጥጥር ኃላፊ  አቶ ፀሐየ  ቅዱስ  በበኩላቸው ማዕከሉ በቲሹ ካልቸር ዘዴ የሚያባዛቸው የሥራሥር፣ ሸንኮራ አገዳና  የፍራፍሬ  ችግኞች የተፈጥሮ ይዘታቸውን  የጠብቁና አኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው  የላቀ ነው ብለዋል።

ኃላፊው አያይዘውም ''ከአንድ ተክል ከቅጠሉ፤ ከግንዱና ከሥሩ ሴል ማለትም ህዋስ  በመውሰድ የተለያዩ ሆርሞኖችን በማሳደግ ከበሸታ ነፃ የሆነ ችግኝ በማውጣት በአጭር ጊዜ እንዲባዛ እያደረግን እንገኛለን ብለዋል''።

''ከማዕከሉ በቲሹ ካልቸር የተባዙ የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ፣ በሽታን የመቋቋም አቅም  ያላቸውና ቶሎ የሚደርሱ 17 ሺህ የአገዳ ችግኞችን ወስደን እያለማን  እንገኛለን''  ያሉት ደግሞ  በትግራይ ምዕራባዊ ዞን የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ  ከፍተኛ የሕዝብ  ግንኙነት ባለሙያ አቶ መልዓኩ ካሕሱ ናቸው።

ችግኞቹ  በምርታማነታቸው የታወቁ ዘጠኝ ዓይነት ዝርያ ያላቸው ሲሆኑ በ144 ሄክታር  መሬት ላይ ተተክለው በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የአገዳ ዝሪያዎቹ አሁን ለቆረጣ በመድረሳቸው በአንድ ሺህ ሄክታር መሬት ለማሰፋፋት በዝግጅት ላይ ነን ብለዋል።

በሙዝ ልማት የተሰማሩት ባለሀብት አቶ ኪዳነ ተኽለ በበኩላቸው ከማዕከሉ ሦስት ዓይነት ዝሪያ ያላቸው 100 የሸንኮራ አገዳ ችግኞችን ወስደው በማልማት ላይ መሆናቸው ተናግርዋል።

የትግራይ እርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚዛን አማረ እንደገለጹት ማዕከሉ በቲሹ ካልቸር የሚያባዛቸው የሥራሥር፣ የአገዳና የፍራፍሬ ችግኞች ጤንነታቸው፣ ደህንነታቸውና ምርታማነታቸው ተረጋግጦ ከምርምር ማዕከላት የተለቀቁ ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም