በፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ለመሆንና ላለመውረድ የሚጫወቱ ክለቦች ነገ ይፋለማሉ

58
አዲስ አበባ ሰኔ 29/2010 በ29ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስድስት ጨዋታዎች ነገ በእኩል ሰዓት ይደረጋሉ። የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ የወንዶች እግር ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሊጠናቀቅ ነገ ከሚደረጉ ጨዋታዎች ውጪ የአንድ ሳምንት ጊዜ ይቀረዋል። ሻምፒዮን ለመሆንና ላለመውረድ ከፍተኛ ትንቅንቅ ውስጥ ያለው ፕሪሚየር ሊጉ ነገ ስድስት ጨዋታዎች የሚደረጉበት ሲሆን ሁሉም ጨዋታዎች ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በክልል ሜዳዎች ይደረጋሉ። ከፕሪሚየር ሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ ከሚወርዱ ሶስት ክለቦች መካከል ወልዲያ እግር ኳስ ክለብ ብቻ መውረዱን ሲያረጋግጥ ቀሪ ሁለት ክለቦች ገና አልታወቁም። በዚህ የወራጅነት ስጋት ውስጥ ደግሞ አርባ ምንጭ ከተማ ፣ወላይታ ድቻ ፣ድሬዳዋ ከተማ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ ሀዋሳ ከተማ እና መከላከያ ይገኙበታል። ምንም እንኳ ከነገው ጨዋታ ውጭ የ30ኛ ሳምንት ጨዋታ ቢኖርም ነገ የሚመዘገቡ ውጤቶች ሻምፒዮን ለመሆንና ከፕሪሚሪየር ሊግ የሚወርዱ ክለቦች ፍንጭ የሚሰጥ ይሆናል። ሊጉን በእኩል 51 ነጥብ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እየመራ ያለው ጅማ አባጅፋር ወደ ደቡብ ተጉዞ የወራጅነት ስጋት ካለበት ወላይታ ድቻ ጋር  የሚያደረገው ጨዋታ በእጅጉ ተጠባቂ ነው። በተመሳሳይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አዳማ ተጉዞ ከአዳማ ከተማ ጋር የሚጫወት ይሆናል። በሂሳብ ስሌት መሰረት ሻምፒዮን ለመሆን ዕድል ካላቸው አራት ክለቦች መካከል ኢትዮጵያ ቡናና መቀሌ ከተማ ይገኙበታል። ኢትዮጵያ ቡና ወደ ጎንደር አቅንቶ ከፋሲል ከተማ ጋር የሚጫወት ሲሆን መቀሌ ከተማ ደግሞ በሜዳው ኢትዮ ኤሌክትሪክን ያስተናግዳል። ሐዋሳ ከተማ በሜዳው ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን ሲያስተናገድ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ አርባምንጭ ከተማን ያስተናግዳል። ከ29ኛ ሳምንት ከሚደረጉ ስምንት ጨዋታዎች መካከል ሁለቱ ትናንት የተደረጉ ሲሆን በሰበታ ስታዲየም ደደቢት ከወልዲያ ከተማ ጋር ያደረጉት ጨዋታ ያለምንም ግብ  ሲጠናቀቅ በይርጋለም ስታዲየም ሲዳማ ቡና መከላከያን አስተናግዶ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባጅፋር ተመሳሳይ 51 ነጥብ እና 19 ግብ ክፍያ ያላቸው ቢሆንም በፕሪሚየር ሊጉ ብዙ ጎል ባገባ በሚለው ህግ ቅዱስ ጊዮርጊስ አንደኛ ጅማ አባጅፋር ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል። ኢትዮጵያ ቡና በ47 ነጥብ ሶስተኛ፤ መቀሌ ከተማ ደግሞ በ46 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዘዋል። ወላይታ ድቻ፣ አርባምንጭ ከተማና መውረዱን ያረጋገጠው ወልዲያ ከተማ በቅደም ተከተል ከ14 እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ። የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የጅማ አባጅፋር ተጫዋች ናይጄሪያዊው ኦኪኪ አፎላቢ በ17 ግቦች ሲመራ፣ ናይጄሪያዊው የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች ሳሙኤል ሳኑሚ በ13 የደደቢቱ ጌታነህ ከበደና የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በ12 ግቦች ይከተላሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም