አስተዳደሩ የግብር ክፍያ ማሻሻያ አደረገ

115

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18/2012 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ለ10 ዓመታት ያልተከፈለ ፍሬ ግብር ወለድና መቀጫ እንዲቀር መወሰኑን አስታወቀ።

የአከፋፈል ሥርዓቱ ላይ ጥናትን መሠረት ማድረጉንም አመልክቷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ ዛሬ ቢሮው በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ የሚስተዋለውን የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ተከትሎ የታክስ እዳ ማቅለያና ስረዛ በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ወለድና መቀጫው እንዲቀር የተወሰነው ከ1997 እስከ 2007 አ/ም መከፈል በነበረበት ግብርና መቀጫ ላይ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል።  

ይህም የንግድ ትርፍ ፣ ከሸማች የሚሰበሰብ ተጨማሪ እሴት ታክስ ፣ የኪራይ ገቢ ግብርና የደሞዝ ገቢ ግብር ይሰበሰብ እንደነበር ኃላፊው አብራርተዋል።  

የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ በንግድና መሰል እንቅስቃሴ ላይ መቀዛቀዝ መከሰቱን የተናገሩት አቶ ሺሰማ፣ በዚህም የታክስ አከፋፈሉን በጊዜያዊነት በማሻሻልና በመሰረዝ ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑ በፌዴራል ደረጃ የሚተገበረውን የዕዳ ቅነሳ መመሪያ በአስተዳደሩም እንደሚተገበር  ተናግረዋል።

በዚህም የግብር ከፋዮችን ዓይነቶችና ዘርፎች በማመጣጠን በመመሪያው ላይ ጥናት መካሄዱን ኃላፊው አብራርተዋል።      

ከሸማቾች የሚሰበሰብ ተጨማሪ እሴት ታክስ፣የንግድ ትርፍ፣የኪራይ ገቢ ግብርና የደሞዝ ገቢ ግብር ማሻሻያ እንደተደረገባቸው አመልክተዋል።

በዚህም ከ1997 እስከ 2007 የነበረው የግብር ዘመን ፍሬ ግብር፣ወለድና መቀጫ በጠቅላላ እንዲቀር ተወስኗል ነው ያሉት።   

ባለፈው ዓመት ተጀምሮ ያልተጠናቀቀና በይርጋ ያልቆመ ኦዲትም በዚህ ሂደት እንደሚያልፍና እንደሚቋጩ ነው።

እንደ አቶ ሺሰማ ገለጻ ከ2008 እስከ 2011 የግብር ዘመን ያሉትን ደግሞ ወለድና ቅጣቱን በማንሳት ፍሬ ግብሩን ብቻ ይሰበሰባል።        

የፍሬ ግብርን በአንድ ጊዜ ለሚከፍሉ 10 በመቶ የማበረታቻ ቅናሽ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

በዚህ የጊዜ ገደብ 25 በመቶውን ቅድሚያ በመክፈል 75 በመቶውን ደግሞ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከፍሎ ማጠናቀቅ ይገባል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በፍርድ ቤት ክርክርና በግብር ይግባኝ ሂደት ውስጥ የሚገኙ  2 ሺህ 800 ግብር ከፋዮች በማሻሻያው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አቶ ሺሰማ አስታውቀዋል።

ከሶስተኛ ወገን የሚሰበሰብ ግብርን ወይም ቀጥተኛ ያልሆኑ ታክስን በተመለከተ ማሻሻያና ቅናሽ እንደማይደረግ ተናግረዋል።

በቀን ገቢ ግምት ላይ ተመስርተው ግብር የሚከፍሉ የንግድ ገቢ ግብር ከፋዮች ሐምሌ ላይ ማሳወቅ እንደሚጠበቅባቸው ያስረዱት ኃላፊው፤ አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ግን  ገቢያቸው ከተቀዛቀዘበት ጊዜ ጀምሮ ባለው ሂደት በማስላት የሩብ ዓመቱን ንግድ ትርፍ ይነሳላቸዋል ብለዋል።  

በኪራይ ገቢ ግብር ወርሃዊ ገቢያቸው ከ10 ሺህ ብር በላይ በተለይም ለትምህርት ቤቶችና ለአነስተኛና ጥቃቅን ንግዶች ያከራዩ ግብር ከፋዮች በዓመት ከሚያገኙት የኪራይ ግብር ላይ 50 በመቶ ቅናሽ እንደሚደረግ ይፈቀዳል ብለዋል።  

ትምህርት ቤቶቹና የንግድ ሱቆቹን በሚመለከት በቅናሹ የሚካተቱት የሁለት ወራት የኪራይ ክፍያ ፋታ  ሲሰጡ መሆኑንም አብራርተዋል።

የሥራ ግብርን በሚመለከት የተደረገው ማሻሻያ ቤታቸው ተቀምጠው ደሞዝ የሚከፈላቸውን ሠራተኞች እንደማያካትት አቶ ሺሰማ አስታውቀዋል።

በዚህም ከሠራተኞቹ ለአራት ወራት ይሰበሰብ የነበረውን የሥራ ግብር እንደሚያስቀር ገልጸዋል።

በማሻሻያ በዓመት በአስተዳደር ደረጃ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የሚያጣ ሲሆን፣ ከውዝፍ ክፍያ ደግሞ 4ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እንደሚከስር ተገልጿል።  

በአስተዳደሩ በደረጃ ሀ፣ ለና ሐ ደረጃዎች የተከፋፈሉ 340 ሺህ የሚጠጉ ግብር ከፋዮች ይገኛሉ።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም