''መንግሥት ለኢትዮጵያ ብልፅግና በቁርጠኝነት ይሰራል'' --ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ

56

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18/2012 (ኢዜአ) መንግሥት ለኢትዮጵያ ብልፅግና በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ አረጋገጡ፡፡

ዜጎች አዲሲቱን ኢትዮጵያ ለመገንባት በጋራ እንዲነሳሱ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በማህበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው ላይ  ባሰፈሩት  መልዕክት  መንግሥት  አገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ጥረቱን አያቋርጥም።

''ኢትዮጵያውያን ብልጽግና ይመጥናቸዋል ፤ ይገባቸዋልም''  ያሉት  ዶክተር ዓቢይ፣''የእኔ አስተዳደርም ለዚህ መሳካት በቁርጠኝነት ይሠራል'' በማለት  ጽፈዋል።

ሰዎች ያለፍንበትን የታሪክ ውጣ ውረድ መርሳት እንደሚያጋጥማቸው አውስተው፤የአካባቢን ፣የአኗኗርን ፣ የከተሞችንና የአገርን ሁኔታ በማየት ''ከዚህ የተሻለ  አይገባንም ፣  ቅብጠት ነው ፣  ለድኻ ይሄ መች አነሰው ብለን እንቀጥላለን'' ብሎ መቆም እንደማይገባ አመልክተዋል።''በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ በቤተ መንግሥቱ ቅጽር ግቢና በከተሞች እየተለወጡ ያሉ ነገሮች ለራስ ከፍ ያለ ቦታ እንድንሰጥ ያስችሉናል'' ብለዋል።

''ከጥቂት ዓመታት በፊት በነዚህ በሮች ያለፉ ኢትዮጵያውያን በግቢው  ሕይወት  ለመዝራት  የተሠራውን የፈጠራ ችሎታና ጉልበት ሳያደንቁ አያልፉምም'' በማለትም ሐሳባቸውን አስፍረዋል፡፡

በአንድነት የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ ለመገንባት በዓላማ ፣ በሐሳብና በትጋት እንነሣ ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም