የክፍያ መመሪያን ተግባራዊ ባላደረጉ 4 የግል ትምህርት ቤቶች የእውቅና ፍቃዳቸው ታገደ

95

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18/2012(ኢዜአ) የኮረና ቫይረስ ስርጭት መስፋፋትን ተከትሎ መንግስት ያስቀመጠውን የግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ መመሪያ ተግባራዊ ባላደረጉኑ አራት ትምህርት ቤቶች ለአንድ አመት የእውቅና ፍቃዳቸው መታገዱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስተወቁ።

የከተማ አስተዳደሩ  የትምህርትና ስልጠና ጥራት ሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ባለስልጣን ዋና ስራአስኪያጅ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ እንደገለጹት፤ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነው የኮረና ቫይረስ መስፋፋትን ተከትሎ የትምህርት ሚኒስቴር ከመጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ መወሰኑ ይታወቃል።

በመሆኑም በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች የገጽ ለገጽ የትምህርት አገልግሎታቸውን እንዲያቋርጡ፣ የአገልግሎት አሰጣጣቸውንም በተለያዩ መንገዶች እንዲያከናውኑ እና የሚያስከፍሉት የአገልግሎት ክፍያም ከ50 እስከ 75 በመቶ እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል፡፡

የወጣው መመሪያ ተግባራዊ መሆኑን ለማረጋገጥ በተደረገ ክትትል አብዛኞቹ የግል ትምህርት ቤቶች በመመሪያው መሰረት ተገቢውን ክፍያ በማስከፈል እንደሆኑና በሌላ በኩል ደግሞ 21 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ከመመሪያው ውጪ ተገቢ ያልሆነ ክፍያ በመጠየቃቸው በአንድ ሳምንት ውስጥ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በዚህም 17 ትምህርት ቤቶች ማስተካከያውን ተግባራዊ ማድረጋቸውን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ቀሪዎቹ 4 ትምህርት ቤቶች ግን የክፍያ መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ ፍቃደኛ ስላልሆኑ በ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን አገልግሎት እንዳይሰጡ ለአንድ አመት እውቅና ፍቃዳቸው መታገዱን አስታውቀዋል፡፡

ትምህርት ቤቶቹም  በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኙት ለምለም እና ሮማን ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የካ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ስሪ ኤም አካዳሚ እና አራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ገነት መሰረተ ክርስቶስ ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን ወይዘሮ ሸዊት ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም