የፓርቲው አመራሮች በመቂ አካባቢ የሚገኝ የችግኝ ጣቢያና የፓፓዬ ልማት ክላስተርን ጎበኙ

57

አዲስ አበባ ግንቦት 18/2012 (ኢዜአ) የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን መቂ አካባቢ የሚገኝ አንድ የችግኝ ጣቢያና የፓፓዬ ልማት ክላስተርን ጎበኙ። የአመራሮቹ ጉብኝት በክልሉ ሌሎች አካባቢዎችም እንደሚቀጥል ተመልክቷል። 

መቂ አካባቢ የሚገኘው "ፍሎራ ጀግ" የተባለው የችግኝ ጣቢያ በአንድ የግል ባለሀብት የሚንቀሳቀስ ሲሆን በየዓመቱ የተለያዩ ችግኞችን አልምቶ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች በተመጣጣኝ ዋጋ ያከፋፍላል።

በጉብኝቱ ወቅት የፍሎራ ጀግ ባለቤት አቶ በየነ ያለው ለኢዜአ እንደገለጹት የችግኝ ልማት ሥራው  እየተከናወነ ያለው በ2 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ላይ ነው።

የችግኝ ጣቢያው በመላ አገሪቱ ለሚገኙ ችግኝ ፈላጊ አርሶ አደሮች አንዱን በ60 ሳንቲም እያከፋፈለ መሆኑንም ተናግረዋል።

በየዓመቱ ከ70 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ የአትክልትና የፍራፍሬ ዝርያ ችግኞች ለአርሶ አደሮች እንደሚከፋፈልም ነው ያመለከቱት።

በዚሁ አካባቢ የሚገኘው የፓፓያ ልማት ክላስተርም በፓርቲው አመራሮች ተጎብኝቷል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አላኬ ሲንቢሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት አርሶ አደሮቹ ያመረቱትን ፍራፍሬ የሚሸጡበት የገበያ ሥፍራ በአዲስ አበባ ተመቻችቶላቸዋል።

በዘርፉ ልማት የተሰማሩ 105 አርሶ አደሮች በተያዘው ዓመት ወደ ባለሀብትነት መሸጋገራቸውንም ጠቁመዋል።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትን በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በጉብኝቱ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማን ጨምሮ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ሌሎች የፓርቲው አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም