በአምቦ ከተማ ከ260 ለሚበልጡ የተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ

54

አምቦ ግንቦት 18/2012 ( ኢዜአ ) በአምቦ ከተማ ከ260 ለሚበልጡ አቅመ ደካሞችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች የምግብ እህልና ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉን ያደረገው የአምቦ ብርሃነ ወንጌል መጥመቃዊያን ቤተክርስቲያን የልጆች ልማት ፕሮጀክት ነው።

የፕሮጀክቱ ዳይሬክተር አቶ ሰኚ ዳቢ እንዳሉት በኢትዮጵያ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ተከትሎ እንቅስኃሴ በመገደቡ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች ለችግር ተጋልጠዋል።

ዛሬ ድጋፍ ያደረጉት ከ220 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የበቆሎ፣ ምግብ፣ ዘይት እና ሳሙና ነው።

በቀጣይም የኮሮና ቫይረስ ከኢትዮጵያ እስኪወገድ ድረስ ፕሮጀክቱ የጀመረውን ድጋፍ  አጠናክረው እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

የአምቦ ከተማ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ሙሊሳ ፈዬራ በበሽታው ምክንያት የተቸገሩ ወገኖችን ለማገዝ ሌሎችም ድርጅቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል በከተማው ኪሶሴ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ቀበኔ ኦላኒ ድርጅቱ ከዚህ በፊትም ችግረኛ ቤተሰቦቸውን በመደገፍና የልጆቻቸውን የትምህርት ወጪ በመሸፈን ሲያግዛቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁንም ላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

በጀበና ቡና ንግድ ስራ ይተዳደሩ የነበሩት በአምቦ የሊበን ሜጫ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ብርሃን መንግስቱ በበኩላቸው በበሽታው ምክንያት ገበያ በማጣት ለችግር ተጋልጠው እንደነበርና ዛሬ በተደረገላቸውም ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በሆመቾ አሙኔሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ የደጀን ክፍለ ጦር ሁለተኛ ብርጌድ የአንደኛ ሻለቃ አዛዥ አባላት 45 ኩንታል ዱቄት በከተማዋ ለሚገኙ ለ180 አቅመ ደካሞች ማበርከታቸውን የሻለቃው ምክትል አዛዥ ሻለቃ ውዱ አራጋው ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

የአምቦ ከተማ አስተዳደር ከንቲባና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስተባበሪ  አቶ ሳህሉ ድርብሳም ድጋፉን ላደረጉት ተቋማት የበጎ አድራጎት ስራ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም