በደቡብ ክልል ለግብርና ባለሙያዎች 10 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የኮሮና መከላከያ ቀሳቁስ ተሰራጨ

192

ሐዋሳ፣ ግንቦት 17/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ለሚገኙ የግብርና ልማት ባለሙያዎች ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የኮሮና መከላከያ ቁሳቁስ ተሰራጨ።

ግብአቱን  ያሰራጩት የደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት  ቢሮና የክልሉ እንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮዎች ናቸው።

 ቢሮዎቹ ከራሳቸውና ከተለያዩ አጋር አካላት ያገኙትን ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኮሮና መከላከያ ቁሳቁስ ዛሬ ለግብርና ልማት ባለሙያዎች  ማሰራጨታቸውን ጠቁመዋል።

በርክክቡ ወቅት ሁለቱን ቢሮዎች ወክለው ንግግር ያደረጉት የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃበት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ እንዳሉት በኮሮና ቫይረስ መከሰት የተነሳ እንቅስቃሴዎች በመገደባቸው ግብአት አቅርቦትና ኤክስቴንሽን ሥርዓት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ መጥቷል።

ችግሩን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት የግብርና ባለሙያዎች ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ቅድሚያ ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸው ገልጸው፤ ይህን ታሳቢ በማድረግ ቁሳቁሶቹ መሰራጨታቸውን ገልጸዋል።

የተሰራጩት ቁሳቁሶች ሳኒታይዘር፣የፊት መሸፈኛ ጭንብልና ሳሙና  ሲሆን በክልሉ ሁሉም ቀበሌዎች ለሚገኙ 20 ሺህ 345 የግብርናና የእንስሳት ባለሙያዎች የሚዳረስ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በተያዘው ዓመት በኮሮና፣በበረሐ አንበጣና በመሬት ናዳ ምክንያት ከ24 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የምርት እጥረት ሊከሰት እንደሚችል ትንበያዎች እንዳሉም ገልጸዋል።

በመሆኑም ከዚህ ቀደም እንደተለመደው ባለሙያዎች ቁሳቁሶችን በመጠቀምና ርቀትን በመጠበቅ የምናጣውን የምርት እጥረት ለማካካስ በሚያስችል መልኩ ለአርሶ አደሩ የሚያደርጉትን  የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያጠናክሩ  ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ቁሳቁሶቹን ተደራሽ ለማድረግ በክልሉ የሚገኙ የሁሉም ዞኖች ተወካዮች ከቢሮ  ኃላፊዎቹ ተረክበዋል።

የወላይታ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ታዲዮስ ባንጫ ድጋፉን ከተረከቡ በኋላ በሰጡት አስተያየት የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ ለልማት ጣቢያ ሠራተኞች የሚሰጡ ትኩረቶች ወሳኝ ናቸው።

በተለይ በዚህ ጊዜ በሰራተኞቹ ባለው የኮሮና መከላከያ ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ሠራተኛውን በአግባቡ ለማሰማራት ተቸግረው መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ረገድ ተፈጥሮ የነበረውን መዘናጋት ለመቅረፍና በስነልቦና  ባለሙያዎቹን ለሥራ ለማነሳሳት ድጋፉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል ።